ለከተማው ዕድገት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለመቅረፍ የአከባቢው ህብረተሰብ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

ለከተማው ዕድገት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለመቅረፍ የአከባቢው ህብረተሰብ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ የካቲት 27/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለከተማው ዕድገት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን በመቅረፍ ሁለንተናዊ ልማትና ሠላም ለማረጋገጥ የአከባቢው ህብረተሰብ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የወላይታ ዞን አስተዳደር አስታውቋል።

በወላይታ ዞን ቦዲቲ ከተማ በአከባቢው ልማትና ዕድገት ዙሪያ ከተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የሚመክር መድረክ ተካሂዷል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ፎላ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ መንግስት የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የጀመራቸውን ጠንካራ ሂደት ከግብ ለማድረስ የህዝቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፥ የከተማውን ዕድገት ለማረጋገጥ በየዘርፉ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በወቅቱ ተጠናቅቀው ለህዝቡ አገልግሎት እንዲውል ክትትልና ድጋፍ መቋረጥ የለበትም ሲሉ ተናግረዋል።

የሚሰሩ የልማት ሥራዎችን የጥራትና ደረጃ በተመለከተ ችግሮች ሲፈጠሩ የከተማው ህዝብ ለሚመለከተው አካል ጥቆማ መስጠት እንዳለበት ዋና አስተዳዳሪው አሳስበዋል።

በከተማው አስተማማኝ ሰላምን ለማስፈን ከፀጥታ አካላት ጋር ያለው የህብረተሰቡ ጠንካራ አብሮነትና ተሳትፎ እንዳይለያቸው ገልጸው፥ ህገወጥ ነጋዴዎችን በመቆጣጠር ህጋዊ የግብይት ስርዓትን ለመዘርጋት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክሮ መቀጠል አእንዳለበት አሳስበዋል።

የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሳምነው አይዛ የከተማውን ዕድገት በማረጋገጥ ከሌሎች ያደጉ ከተሞች ተረታ ለማሰለፍ የጋራ ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።

በአንዳንድ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ህዝቡን የሚያማርሩ የአገልግሎት አሰጣጥ መኖሩን የጠቆሙት ኃላፊው፥ ችግሮቹ የመልካም አስተዳዳሪ ጥያቄ ሆነው በመቀጠላቸው ህዝቡ በመንግሥት ላይ ያለውን አመኔታ እንዲያጣ እያደረገ ይገኛል ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል።

በተለይ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ላይ ያሉ ጫፍ የወጡ አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለአብነት በማንሳት ለተገልጋዩ ህዝብ አገልግሎትን በገንዘብ ለመስጠት የሚጥሩ አንዳንድ ባለሙያዎች ላይ ተገቢ እርምጃ በመወሰድ ከህግ አግባብም እንዲጠየቁ ማድረግ አለበት ብለዋል።

እነዚህንና መሰል ጉዳዮች ለመፍታትና የህዝቡን አቤቱታ በመስማት አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የከንቲባ ችሎት በከተማው መዘርጋት እንዳለበትም አሳስበዋል። ህገወጥ ግንባታ፣ የመሬት ወረራና የመሳሰሉ ተግባራት ለመከላከል ህዝቡ ከመንግሥት ጋር ተቀናጅተው መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።

የቦዲቲ ከተማ ከንቲባ አቶ እሸቱ ታደሰ በበኩላቸው የህዝቡን እኩል የመልማት ጥያቄዎች ለመፍታት የተጀመሩ የልማት ሥራዎች እንዲጠናቀቁ ተገቢ ክትትልና ቁጥጥር እናደርጋለን ብለዋል።

ከተማውን ውብና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ በትኩረት እንሰራለን ያሉት የከተማው ከንቲባ፥ ህብረተሰቡም የበኩሉን አስታውጾ እንዲያበረክት ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፡ በቀለች ጌቾ – ከዋካ  ጣቢያችን