የልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮችን በየደረጃው ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ

የልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮችን በየደረጃው ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ የካቲት 26/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሆሳዕና ከተማ የሚስተዋሉ የልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮችን በየደረጃው በመለየት፥ ለመፍታት እንዲቻል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በትኩረት ሊሰራ ይገባል ሲሉ የሀድያ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ማቲዎስ አኒዮ ገለጹ።

የዞኑ አዳዲስ ሥራ አስፈፃሚዎች ከሆሣዕና ከተማ  አመራር አካላት ጋር የትውውቅ መድረክ አካሂዷል።

የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ማቲዎስ አኒዮ በሆሳዕና ከተማ በርካታ የልማት ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመው፥ ከተማውን ከትልልቅ ከተሞች ተርታ ለማሰለፍ ህብረተሰቡ በልማቱ ላይ በንቃት እንዲሳተፍ በቅንጅት መስራት ይጠበቃል ብለዋል።

ከላይ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ የተግባርና የስነምግባር ወጥነትን በማጠናከር በቅንጅት መስራት ወሳኝ እንደሆነም አንስተዋል።

በየጊዜው ከከተማ አልፎ የዞኑም ከፍተኛ ችግር የሆነውን የሆሳዕና ከተማ ህገወጥ የመሬት ወረራ መታገልና በድርጊቱ ላይ የተሳተፉ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በከተማው የተለያዩ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር የመሬት ዝግጅት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

በከተማው በአንዳንድ መንደሮች የአረንጓዴ ልማት ስፍራዎች ወደ ግለሰቦች እየተቀየሩ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፥ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በሌሎች ክልል ከተሞች የሚታዩ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋት መፍጠን ያስፈልጋልም ብልዋል።

በከተማው የሚስተዋሉ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮችን ወደ ፀጥታ ማዋቅሮች ብቻ ከመወርወር ይልቅ  የስጋት ቀጠናዎችን በመለየት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ዋና አሰተደደሪው ገልጸዋል።

የከተማውን የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትና ፍላጎት ለማሟላት በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ ስራዎች መፍጠን እንደሚገባቸውም አቶ ማቲዎስ ተናግረዋል።

በየሴክተሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቶችን ማዘመን ይገባል ያሉት አቶ ማቲዎስ በየጊዜው በማህበራዊ ሚዲያ የሀሰተኛና የጥለቻ ንግግሮችን በማሰራጨት የህብረተሰቡን ሰላምና ደህነት፣ የልማት ተግባራትን፣ አንድነትና መግባባትን የሚያውኩ አካላትን በጋራ መከላከል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በከተማው የሚስተዋሉ የልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮችን በየደረጃው መለየትና መፍታት እንደሚገባም አቶ ማቲዎስ አሳስበዋል።

የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሊሬ ጀማል እንዳሉት በከተማው ከህብረተሰቡ የሚነሱ  የልማትና መልካም አሰተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የውሃና የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት ለማጠናቀቅ  እየተሰራ ይገኛል።

በየደረጃው የገቢ ምንጮችን በመለየት ገቢን አሟጦ ለመሰብሰብም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አመላክተዋል።

የከተማ ግብርና ልማትን በማጠናከር የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥም ባለፈ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት በየአካባቢው የሰንበት ገበያ  የማስፋፋት ስራ እየተሰራ እንደሆነም ከንቲባው ገልጸዋል።

አንዳንድ የመድረኩ ተሳታፊ አመራር አካላት በሰጡት አስተያየት የሀሳብና የአመለካከት ልዩነቶችን በማጥበብ ለጋራ ውጤታማነት  በአመራር ስነምግባር ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል ።

በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት በመድረኩ ላይ የተነሱ ጠንካራ ጎኖችን በማጠናከርና ጉድለቶችንም በማረም ከተማውን ለህብረተሰቡ ምቹና ማራኪ ለማድረግ ሊሰራ ይገባል ብለዋል ።

በመድረኩም  የመልካም አስተዳደር፣ የመሬት ወረራ፣ የህግ በላይነት ጠንካራ ያለመሆን፣ የማህበራዊ ሚድያ አጠቃቀም ጉድለት፣  ኑሮ ውድነትን በጋራ አለመተጋል፣ የመሰረተ ልማት ተደራሽነት ችግር፣ የፅዳትና ውበት ጉዳይ ትኩረት ያለመስጠት፣ የገቢ አሰባሰብ ሂደት ያለማጠናከር የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው በየደረጃው በሚገኙ ባለድርሻ አካላት ምላሽና መብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ዘጋቢ: ተመስገን ታደለ – ከሆሳዕና ጣቢያችን