በጤናው ዘርፍ ለህብረተሰቡ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት እየሠራ እንደሚገኝ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት አስታወቀ

በጤናው ዘርፍ ለህብረተሰቡ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት እየሠራ እንደሚገኝ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት አስታወቀ

በጋሞ ዞን ብርብር ከተማ አስተዳደር የብርብር ጤና ጣቢያን ወደመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ለማሳደግ ሀብት የማሰባሰቢያ ባዛር እየተካሄደ ይገኛል።

በዕለቱም ለሆስፒታሉ ግንባታ የሚውል ከ11 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡ ተገልጿል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ እና የርዕሰ መስተዳድሩ የዕለቱ ተወካይ ወ/ሮ ሰናይት ሠለሞን ፤ በገቢ ማሰባሰቢያ ባዛሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት የክልሉ መንግሰት ጤናው የተጠበቀና አምራች ዜጋ እንዲኖር አስፈላጊውን ሁሉ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

መንግስት ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ እየሠራ እንደሚገኝ የገለጹት ወ/ሮ ሰናይት ግንባታው የተጀመረውን የብርብር የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ለማጠናቀቅ የክልሉ መንግስት የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ በመጠቆም ህብረተሰቡም እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

ከመሠረተ ልማት ጋር ተያይዞ በጤናው ዘርፍ የሚስተዋለውን ውስንነት ለመቅረፍ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሀኑን የገለጹት ደግሞ የጋሞ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባይነህ አበራ ናቸው፡፡

ምክትል ዋና አስተዳዳሪው ያለህብረተሰቡ ተሳትፎ መንግስት ሁሉን ነገር ማሟላት ስለማይችል ህብረተሰቡ እያደረገ ያለው ድጋፍ ወሳኝና አርአያነት ያለው ተግባር እንደሆነ አንስተዋል።

አባቶቻችንና እናቶቻችን ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው የዛሬዋን ሀገር አስረክበዋል ያሉት አቶ አባይነህ አንድነታችንን በማጠናከርና በመተባበር ለሆስፒታሉ ግንባታ አሻራችንን በማሳረፍ ለአገልግሎት ማብቃት ያስፈልጋል ብለዋል።

የብርብር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብርሃም አይካ ህብረተሰቡ በቅርበት የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ለረጅም ዓመታት ሲጠይቅ የነበረ መሆኑን አውስተው የብርብር ጤና ጣቢያን ወደመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ለማሳደግ ህብረተሰቡን በማስተባበርና በማሳተፍ የገቢ ማሰባሰቢያ ባዛር መዘጋጀቱን ገልፀዋል።

ሆስፒታሉ ሲጠናቀቅ 100 ሺህ ለሚሆኑ ለአካባቢው ህብረተሰብ አገልግሎት እንደሚሰጥ ከንቲባው አክለው አስረድተዋል።

ባዛሩን ከብርብር ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን በጋራ እንዳዘጋጁት የገለጹት የምዕራብ አባያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወርቁ ወልዴ፤ የሚሰበሰበው ገቢ የሆስፒታሉን ግንባታ ለማጠናቀቅና የህክምና ቁሳቁሶችን ለማሟላት እንደሚውል ገልጸዋል።

የብርብር ከተማ ነዋሪ ከሆኑት መካከል አቶ ምኖታ ደባልቄ እና ባደገ ባልጣ የከተማው አሰተዳደር ህብረተሰቡ የህክምና አገልግሎት በቅርበት እንዲያገኝ ለማስቻል እየሠራ በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የብርብር ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በቅርበት መሠራቱ በተለይ ለእናቶችና ለህፃናት ጤና መጠበቅ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው የገለጹት ደግሞ ወ/ሮ ፍሬህይወት ባራሪ ናቸው።

በሀብት ማሰባሰቢያ መርሃግብሩ ላይ የዞኑ መዋቅሮች፣ የአካባቢው ተወላጆዎች፣ ነጋዴዎችና የመንግስት ሠራተኛች እንዲሁም ሌሎች የልማት አጋሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ዘጋቢ፡ ከበደ ካሳዬ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን