የማህፀን በር ጫፍ ካንሰርን ለመከላከል ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት ሊወስድ ይገባል ተባለ

የማህፀን በር ጫፍ ካንሰርን ለመከላከል ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት ሊወስድ ይገባል ተባለ

ሀዋሳ፤ የካቲት 23/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) እየተበራከተ የመጣውን የሴቶች የማህፀን በር ጫፍ ካንሰርን ለመከላከል ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት ሊወስድ ይገባል ተብሏል፡፡

የአሪ ዞን ጤና መምሪያ ከየካቲት 25/2016 ዓ.ም ጀምሮ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር መከላከል ክትባት ለመስጠት ለጤና ባለሙያዎች የግንዛቤ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

በስልጠና ከተሳተፉ የጤና ባለሙያዎች መካከል ሲስተር ጋምነሽ ገዛኸኝና ወሳኝ ኃይሌ በጋራ እንደገለፁት በሚሰሩበት አካባቢ የበርካታ እናቶች በማህፀን በር ጫፍ ካንሰር እናቶች ህይወታቸው እያለፈ እንደሚገኝ ገልፀው በቀጣይ የሚሰጠው ክትባት የእናቶችን ህይወት ለመታደግ እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡

በአሪ ዞን ጤና መምሪያ የእናቶችና ህፃናት ዳይሬክተር የክትባት አስተባባሪ አቶ ይሁን ጌሎ እንደሀገር በዓመት ከ7 መቶ ሺህ በላይ ሴቶች በማህፀን በር ጫፍ ካንሰር እንደሚታመሙና ከ3መቶ ሺህ በላይ ሴቶች በበሽታው ህይወታቸውን እንደምያጡ ገልፀው በዞኑም የበርካታ ሴቶች ህይወት እንደሚያልፍ አስታውቀዋል።

የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስ በቀበሌ ጤና ኤክስተንሽኖች አማካኝነት እየተሠራ ካለው የቅድመ መከላከል ሥራዎች በተጨማሪ ከየካቲት 25 እስከ 29/2016ዓ.ም ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሞላቸው ሴት ታዳጊዎች የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ክትባት በዞኑ ሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደር እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል።

የአሪ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ይስሐቅ ቀፃይ በበኩላቸው ከፊታችን ሰኞ ዕለት ጀምሮ በዞኑ ሁሉም አካባቢዎች በዘመቻ መልክ ለሚካሄደው የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ክትባት ዞኑ አስፈላጊውን የግበዓትና ሌሎች ቁሳቁስ ዝግጅት አጠናቆ ወደየ አከባቢው እያጓጓዙ መሆኑን ጠቁመው ማህበረሰቡ ዕድሜያቸው 14 ዓመት የሞላቸው ታዳጊዎች በሙሉ ክትባቱን እንድያገኙ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

 ዘጋቢ፡ መልካሙ ቡርዝዳቦ – ከጂንካ ጣቢያችን