ምክር ቤቶች ከአስፈፃሚ  መሥሪያ ቤቶች ጋር  በቅርበት በመሥራት ለወከላቸው  ሕዝብ ተጠቃሚነት   መሥራት እንዳለባቸው ተገለፀ

ምክር ቤቶች ከአስፈፃሚ  መሥሪያ ቤቶች ጋር  በቅርበት በመሥራት ለወከላቸው  ሕዝብ ተጠቃሚነት   መሥራት እንዳለባቸው ተገለፀ

ሀዋሳ፡ የካቲት 23/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ምክር ቤቶች ከአስፈፃሚ  መሥሪያ ቤቶች ጋር  በቅርበት በመሥራት ለወከላቸው  ሕዝብ ተጠቃሚነት   መሥራት እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡

በኣሪ ዞን የጂንካ ከተማ አስተዳደር  ምክር ቤት በ2ኛ ዙር 7ኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ጉባኤውን ያካሄደ ሲሆን  358 ሚሊዬን ብር በላይ በጀትም አፅድቋል፡፡

በየደረጃው  የሚገኙ ባለድርሻ አካላትና አስፈፃሚ  መሥሪያ ቤቶች  ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት  ትኩረት እንዲያደርጉ የገለፁት የጂንካ ከተማ አስተዳደር  ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ  ወይዘሮ  አበራሽ አበበ በምክር  ቤቱ ልዩ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይም መልዕክት  አስተላልፈዋል፡፡

የ2016 ዓ.ም የ6 ወር  አፈፃፀም  ሪፖርት ያቀረቡት የከተማው  ከንቲባ  አቶ አስፋው  ዶሪ ቀልጣፋና  ፈጣን አገልግሎት በመስጠት የህብረተሰቡን የልማትና  የመልካም  አስተዳደር  ጥያቄዎችን ለመፍታት  የምክር  ቤቱ አባላት የህዝብ ውክልናቸውን እንዲወጡ  ገልፀው  የከተማ አስተዳደሩም ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ  ከንቲባው  አቶ አስፋው  ያቀረቧቸው የዋና አፌጉባኤ፤ የማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴና የፅህፈት  ቤት ኃላፊዎች  ሹመት በምክር ቤቱ አስተያየት  ተሰጥቶ በሙሉ ድምፅ የፀደቀ ሲሆን ተሿሚዎችም ቃለመሃላ ፈፅመዋል፡፡

አስተያየታቸውን  የሰጡ የምክር ቤት  አባላት  በአስተዳደር፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚው ዘርፍ ተጨባጭ  ለውጥ ለማምጣት  የድርሻቸውን  እንደሚወጡ ገልጸው  ለቀበሌ  ምክር ቤቶች የድጋፍና ክትትል ማዕቀፍ እንዲጠናከር፤ ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እንዲሻሻል፤ በመሬት አስተዳደር  የሚስተዋሉ  ችግሮች እንዲፈቱም ጠይቀዋል፡፡

ጉባኤው የጂንካ ከተማ የመጀመሪያ  ደረጃ ፍርድ ቤት አፈፃፀምን በመገምገም ለከተማ አስተዳደሩ  የ2016 ዓ.ም ማስፈፀሚያ የሚውል  358 ሚሊዬን 11 ሺህ 819 ብር በጀት በማፅደቅ ተጠናቋል፡፡

ዘጋቢ: ተመስገን  አሰፋ – ከጂንካ ጣቢያችን