ከክልሉ አልፎ እንደሀገር ምቹና ጤናማ የአሠሪና ሠራተኞች ግንኙነትና አሠራር እንዲኖር ልዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ተገለፀ

ከክልሉ አልፎ እንደሀገር ምቹና ጤናማ የአሠሪና ሠራተኞች ግንኙነትና አሠራር እንዲኖር ልዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ የካቲት 23/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከክልሉ አልፎ እንደሀገር ምቹና ጤናማ የአሠሪና ሠራተኞች ግንኙነትና አሠራር እንዲኖር ልዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ተገልጿል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ  መንግስት ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ክልላዊ የአሠሪና ሠራተኛ የንቅናቄ መድረክ “ጠንካራ የሥራ ባህልና ምቹ የሥራ ቦታ ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል በአሪ ዞን ጂንካ በተካሄደበት ወቅት ነው ይህ አጽንኦት ተሰጥቶ የገለፀው።

የድመረኩ ተሳታፊዎች ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በግል ደረጃ ቀጥረው የሚያሠሩ ግለሰቦችም ሆነ በተለያዩ ቦታዎች ተንቀሳቅሰው የሚቀጠሩ ዜጎች ደህንነታቸውና ጤንነታቸው የተጠበቀ መሆን እንዳለበት በስፋት በውይይቱ ተነስቷል ።

የግል ሠራተኛና ሥራ  አገናኝ ኤጀንሲዎች በልዩ ጥንቃቄ የዜጎች መብት ባከበረ መልኩ በሀላፊነት ሊሠሩ እንደሚገባም የተገለፀ ሲሆን መልካም የሥራ ግንኙነትና የዜጎች መብት በአግባቡ ሳያከብሩ ጥቅምን ብቻ መነሻ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ተጠያቂ የሚሆኑበት አሠራር በመኖሩ እንዲታረሙ ክትትል ሊደረግ ይገባል ተብሏል።

የቅንጅት አሠራር ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በመድረኩ አጽንኦት ተሰጥቷል።

የውጭ ስራ ስምሪት አግኝተው የሚሄዱ ዜጎች የሙያ ክህሎት ስልጠና አግኝተው ወቅቱን በጠበቀና እንደሀገር በሁሉም አካባቢ እኩል ተጠቃሚነት እንዲኖር መሥራትን ይጠይቃል ተብሏል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ዋኖ ዋሎሌ እንደገለፁት ቅንጅታዊ አሠራሮችን በማጠናከር በሁሉም ዘርፍ ዘላቂ ለውጥ እንዲመዘገብ ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል ብለዋል።

የውጭ ስራ ስምሪት ጤናማ እንዲሆን ፓስ ፖርትን ጨምሮ የኢሚግሬሽን ማዕከል በክልሉ እንዲቋቋም ይደረጋል ሲሉም የቢሮ ሀላፊው ገልፀዋል።

ህገ -ወጥ የሰዎች ዝውውር ችግርን ለመፍታት በሥራ ከሚገናኙ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ችግሩ እንዲፈታ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል ዶ/ር ዋኖ።

 የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍሬድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቦጋለ ፈይሳ በመድረኩ የተላለፉ መልዕክቶች ወደ ተግባር እንዲቀየሩ ሁሉም የባለድርሻ አካላት ሀላፊነት አለበት ሲሉ አሳስበዋል።

በመድረኩ በዘርፉ የተሻለ ውጤትና ለውጥ ያስመዘገቡ የመንግስት ተቋማትና በግል ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሠማሩ አካላት እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን