በ2016 በጀት ዓመት በመጀመሪያ አጋማሽ የሥራ ዘመን የነበሩ ደካማ ጎኖችን በማሻሻል በቀጣይ በጥንካሬ የታዩ ጉዳዮችን ማስቀጠል እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ የካቲት 23/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በ2016 በጀት ዓመት በመጀመሪያ አጋማሽ የሥራ ዘመን የነበሩ ደካማ ጎኖችን በማሻሻል በቀጣይ በጥንካሬ የታዩ ጉዳዮችን ማስቀጠል እንደሚገባ ተገለጸ።
በጌዴኦ ዞን የገደብ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 5ኛ የሥራ ዘመን 2ኛ ዙር 15ኛ መደበኛ ጉባኤ አካሂዷል።
በጉባኤው የከተማው የምክር ቤት፣ የከተማው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እና በከተማ አስተዳደር ሥር የሚገኙ የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የ2016 በጀት ዓመት የሁለተኛ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ የምክር ቤቱ አባላት በተገኙበት ውይይት ተደርጎበታል።
በውይይቱም በግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም የነበሩ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች በስፋት ተገምግሟል።
በመንግሥት ክስ ላይ ትኩረት ያለመሰጠት፣ የሚሰጡ ውሳኔዎችን በሚዲያ አማካኝነት ለህብረተሰቡ ከማሰራጨት ረገድ የሚስተዋሉ ክፍተቶች እና ሌሎችም ጉዳዮች እንደ ውስንነት የተገመገሙ ሲሆኑ የገቢ አሰባሰብ ሂደት፣ የከተማውን ህብረተሰብ በማሳተፍ እየተሠሩ ያሉ የመሰረተ ልማት ሥራዎች እና ለሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ እድል ከመፍጠር ረገድ የተሠሩ ሥራዎች በጠንካራ ጎን የተገመገሙ ጉዳዮች ናቸው።
በተነሱ ጉዳዮች ዙሪያ ምላሽ የሰጡት የገደብ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛ እና ሰምቶ የመወሰን ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ መብራቱ አለማየሁ የመንግስት ክሶች በፍጥነት ውሳኔ እንዳያገኙ ከሳሾች የተጣራ መረጃ አለማቅረባቸው እንቅፋት እንደሚሆን በመግለጽ በተመረጡ ጉዳዮች ላይም የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኝ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ታሪኩ ሮበ ከምክር ቤቱ አባላት በስፋት የተነሳውን የንጹህ የመጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም የመንገድ መሰረት ልማት ለህብረተሰቡ ያለው ፋይዳ የጎላ በመሆኑ የመንገድ ከፈታ ሥራም ሆነ ለጠረጋ ሥራ የውስጥ ገቢያችንን በማሳደግ አቅማችን በፈቀደ መልኩ በቀጣይም አጠናክረን እንሠራለን ብለዋል።
ሁሉም ሥራ አስፈጻሚ አካላት በ2016 በጀት ዓመት በመጀመሪያ አጋማሽ የሥራ ዘመን የነበሩ ደካማ ጎኖችን በማረም ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል ከከተማው ህብረተሰብ ለሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ታደለ በየነ ተናግረዋል።
የመድኃኒት ችግር፣ የመብራት መቆራረጥ እና ሌሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በተመለከተ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ከከተማው ካቢኔ አባላት ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቷል።
ምክር ቤቱ ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ የቀረበው ሪፖርት ሰነድ ሆኖ እንዲቀመጥ በመግባባት ለ2016 በጀት ዓመት በቀረበው ተጨማሪ ረቂቅ በጀት ዙሪያ ከተወያዩ በኋላ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።
ዘጋቢ: እንግዳየሁ ቆሳ – ከይርጋጨፈ ጣቢያችን

More Stories
የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶችን የስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች ለመቅረፍ የተጀመሩ ጥረቶችን ለማጎልበት የጤና አደረጃጀቶችን ሚና ማሳደግ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ
ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመግባት ዕድል ያገኙ ተማሪዎች የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ትምህርታቸው ላይ ብቻ ሊያተኩሩ እንደሚገባ መልዕክት ተላለፈ
የሀዲያ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ለ2018 በጀት ዓመት ከ10 ቢልዮን ብር በላይ በጀት ለተለያዩ የልማት ስራዎች እንዲውል በተገቢው እንደሚሠራ ገለፀ