የሰው ልጅ ነጻነትን የተረጎመበት ዓለም አቀፍ ሰነድ ነው ዓድዋ።

የሰው ልጅ ነጻነትን የተረጎመበት ዓለም አቀፍ ሰነድ ነው ዓድዋ። ይህንን ድል የኪነ ጥበቡ ቤት፣ የከያኒው ልብ “እንዴት ዘመረው? እንዴት ዘከረው?” ብሎ መቃኘት ጠቃሚ በመሆኑ ዓይኖቻችንን ኩለን የታሪካችንን ሰነድ፣ የሰንደቃችንን ግርማ አጥርተን ልናይ እመኛለሁ።

የሰው ልጅ ክቡር፣

ሰው መሆን ክቡር

ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን፤

“ሰው” የሚለው ቃል ሁለንታዊ (Universal) ነው። ዓለምን ሁሉ የሚሞላ ሰፊ ማዕቀፍ ነው፤ “ሰው ክቡር” ስትል ደግሞ የሰው ክብሩ ከነጻነቱ ይጀምራል። በነጻነት መኖር ሰዋዊና ሕሊናዊ ነው። ይህ ሀሳብ የሚወስደን ቶማስ ጀፈርሰን ዋነኛ መርሁ ያደረገው የሰው ልጅ ነጻ ሆኖ የተፈጠረ ፍጡር ነው የሚለውን ጉዳይ አጽንዖት ወደ መስጠት ነው፤ እኔም አባቶቼም፣ ሌሎች ያገሬ ልጆችም በዚህ ስለምናምን ባርነትን እስከ ዛሬ አሻፈረኝ ብለናል።

ዓድዋ የዚያ እምቢታ ማሳያና ውጤት ነው። በገሃድ እንደታየው፣ ለነጻነት ክብር ዓድዋ ላይ “ሰው”ን ሰው ለማድረግ ሰው ሞቷል፤ ለመንፈስ ልዕልና ሕይወቱን በጦር ሜዳ አፍስሷል፤ ደሙን ሜዳ ላይ ደፍቷል።

አዎ፤ በሞት ጥርስ ጫፍ ላይ የተንጠለጠለው የመጨረሻ ተስፋችንን ለማለምለም በቋፍ ላይ የነበረውን ሉዐላዊነታችንን ለማስከበር በጊዜው ቤዛ የሆኑልን አባቶች ሺህዎች ናቸው። እናም ዓድዋ ላይ አንዱ ለሌላው ልዕልና ሞቷል። ወርቅ የሆነ ሰው በእሳት አልፎ፣ አፈር ሆኗል፤ ይህ ሁሉ ግን ሌሎችን ወርቅ አድርጎ ለማኖር ነው።

እጅጋየሁ ሽባባው፣

የተሰጠኝ ሕይወት ዛሬ በነጻነት፣

ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት

ትላለች!

ጸጋዬ ገብረመድኅን ደግሞ “እሳት ወይ አበባ” በሚል መጽሐፉ ላይ እንዲህ ይላል፤

ዓድዋ የዘር አፅመ ርስትዋ

የደም ትቢያ መቀነትዋ

በሞት ከባርነት ስርየት

በደም ለነጻነት ስለት

አበው የተሰውብሽ ለት

ይህም አንጓ ወደ ኋላና ወደፊት የሚያይ፣ የሚያጠነጥን፣ ከመስዋዕትነቱ ሜዳ እስከ ነጻነቱ አፅናፍ የሚተርክ ነው፤ በዚህ አንጓ መስዋዕትነቱ መቆየቱን የሚያሳየው የፈሰሰው ደም ደርቆ ትቢያ ሆኖ፣ ከአፈር ጋር አፈር መሆኑ ነው። የደረቀው ደም ግን ተበትኖ አልቀረም፤ መቀነት ሆኖ ኢትዮጵዊ አንድነታችንን አስጠብቆልናል፤ ሕልውናችንን በታሪክ ዳንዳ ከፍ አድርጎ ሰቅሎታል።

በደም ውስጥ ሕይወት አለ፤ ሕይወት ለነጻነት ተከፍሏል፤ ለባርነት ስርየት ፈስሷል። ምሱን የተቀበለው የዓድዋ ምድር ርስትነቱ ፀንቷል። ቦታው ዓድዋ፣ ኪዳኑ መስዋዕትነት ነው። ሰንደሉ ትውልድ ጤሶ እስከ ዛሬ በሀገርና በዓለም አድማሳት ይናኛል። …ዛሬም ለእኛ የሽቱ ያህል መዓዛ፣ ለማይወዱን ደግሞ የሞት ያህል ክርፋት ሆኖ ይኖራል። አባቶቻችን ጠባሳው ሕመም እንዳይሆን፣ በድል የክብር ቀለም ቀብተው፣ ከፍ አድርገው ሐውልቱን ከታሪክ ጋር ገምደውታል።

ስለዚህም ከያንያኑ ደም ተከፍሎበታል !… ሰው ተከፍሎበታል!… ይሉናል!

ያንን የደም ዋጋ፣ ያንን ታላቅ ተጋድሎ፣ ያንን እንደ ችቦ በታሪክ ውስጥ የሚነድድ ደም እጅጋየሁ ሽባባው እንዲህ ትገልጸዋለች።

በደግነት፣ በፍቅር፣ በክብር ተጠርቶ፤

በክብር ይሄዳል፤ ሰው ሊኖር ሰው ሞቶ።

ድምጻዊ እጅጋየሁ ሽባባው

ዓድዋ ነፍስን ለሌሎች ነፍስ የመስጠት ተዓምር ነው። ይህንን የሚያደርግ ደግሞ የጀግና ልብ ሩቅ ተመልካች ዓይን ነው። የከበረች ምድሩን አሳልፎ የማይሰጥ፤ የነጻነቱ ትዕምርት የሆነው የባንዲራው ቀለም በልቡ የታተመ፤ ስለዚህ ሕልሙ ሀገሩ ፤ ክብሩም ነጻነቱ የሆነ።

ስለ ወገኖቹ በቋያ እሳት አልፎ፤ ነበልባል ሆኖ ነድዶ ሲያበቃ ነበልባሉን በታሪክ አንገት ላይ የድል ጉንጉን አበባ አድርጎ ያጠለቀ፣ የትዝታውን አመድ በታሪክ ገጾች ላይ ወርቃማ ቀለም አጥቅሶ ያሰፈረ፣ ኩሩ ትውልድ መሆኑን ነግረውናል። ይህንን ደግሞ ሴቶች እናቶቻችን ሳይቀሩ በገቢር አሳይተውታል። በጦር ሜዳ ከተሰለፉት ሌላ ለቁስለኞች ውሃ በማቅረብ፣ ቁስላቸውን በመጠገን፣ አዝማሪዎቹ ጀግኖችን በማደፋፈር፣ ጀግንነታቸውን አሳይተዋል።

ሲጠቀለል የዓድዋ ጦርነት መነሻ ምንጩ “አትንኩን!” ነው። “አትንኩን” ቢሆንማ ቤቱ ተቀምጦ ባልተነካ!…”አትንኩን!” ያለው ግን ትግራይ ያለው ወገኑ ሲነካ ስላመመው ነው፤ ሰሜኑ፣ ደቡቡ፣ ምሥራቁ፣ ምዕራቡ ሲነካ “አትንኩን!” ብሎ በቁጣ ቤቱን ጥሎ ወጥቷል። ይህ ውለታ ያልጠፋት ከያኒ እንዲህ ታቀነቅናለች፡-

የተሰጠኝ ሕይወት ዛሬ በነጻነት፣

ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት፣

ስንት ወገን ወደቀ በነጻነት ምድር

ትናገር ዓድዋ ትናገር ትመስክር!

ትናገር ዓድዋ ትናገር ሀገሬ

እንዴት እንደቆምኩኝ ከፊታችሁ ዛሬ።

. . . በዘይቤ አሽቆጥቁጣ ዓድዋን ለእማኝነት ትጋብዛለች።

በዛሬው የነጻነት ሰንደቅ ስር በሚፍለቀለቅ የነጻነት ዜማ፣ በሀገር አደባባዮች ላይ ለመቆም ትናንት የተከፈለ ውድ ዋጋ አለ። ዛሬ እሸት እሸት ለሚሸትተው ተስፋ ትናንት የከሰለ የወገን አጽም ነበር። በዚያ ዐውደ ውጊያ የብዙ ጀግኖች አጥንት እንደ ችቦ ነዷል፤ ያ የብርሃን ወጋገን ግን ዛሬ በጸና ሥነልቡናዊ ማንነትና ክብር ሁላችንንም አቁሞናል።

እጅጋየሁ ሽባባው ለዚህ ምስክሯ የዓይን እማኟ ዓድዋ ናት እያለችን ነው።… ዓድዋ ተራራው -አድዋ – ሰማዩ ፣ ሰማዩን የሳመው የተራራው ከንፈር … ከውስጡ የሚመነጨው የትዝታ ገሞራ – ፊታውራሪ ገበየሁ – ገብቶ ሲነድድ – መዓዛው ለዛሬ ጣፋጭ- የነጻነት ዜማ … የባርነት ስርየት ነው። የመትረየስ እሳት ምላስ ያነደደው ተራራ፣ አፈሩን የዛቀው መድፍ ግራና ቀኙን የተጎሰመው ነጋሪት ድምጽ ያሸበረው ቁጥቋጦ የተሳከረውን ድብልቅልቅ ዋጋ፣ ስሌቱን የታሪክ ድርሳናት ብቻ ሳይሆኑ ዓድዋ ራሱ ይተርከው ብላለች።

ከያኒዋ “ትናገር … ትናገር! ያለችው በአጽንዖት ነው። ያኔ የነበረችው፣ ዛሬም በጉያዋ ስር ያንን ተዓምር ያቀፈችው እርሷ ናት!… የነደደ ፊቷ … የከሰለ ልቧ … ያንን ጠባሳ በእንባ እያጠቀሰ ሳይሆን በሳቅ እየፈካ ይናገረዋል!… እንባችንን አባቶቻችን አልቀሰው በሳቅ መንዝረው ሰጥተውናል! አፈር ሆነው ወርቅ አውርሰውናል!

ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን እንዲህ ይላል፤

ዓድዋ ሩቅዋ

የአለት ምሶሶ አድማስ ጥግም

ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋ

የማይፈርስ ምሶሶ አድርገዋት ያለፉት፣ የማይደረስበት አድማስ አድርገው ታሪኳን የጻፉት ኩሩ ትውልድ ነበሩ። እንደ ጧፍ የነደዱ የማይገሰስ ክብር፣ የማይናድ ገድል ጽፈው ያለፉ!…እነዚህ ጀግኖች ግን በየአቅጣጫው የተመሙት ሞተው እናን በክብር ለማኖር ነው።

እናም እጅጋየሁ ሽባባው ዓድዋን እንዲህ ታሞካሻታለች፤

ዓድዋ ዛሬ ናት ዓድዋ ትናንት

መቼ ተረሱና የወዳደቁት

ምስጋና ለእነሱ የዓድዋ ጀግኖች

ለዛሬ ነጻነት ላበቁኝ ጀግኖች

የጥቁር ድል አምባ ዓድዋ

አፍሪካ እምዬ ኢትዮጵያ

ተናገሪ የድል ታሪክ አውሪ

ስለ ዓድዋ በዜማ አቀንቅና አላበቃችም፤ ስለ ዋነኞቹ ጀግኖች አውስታለች፤”ምስጋና!” ብላ የክብር ዘውድ ደፍታላቸዋለች፤ አበባ ጉንጉን አጥልቃላቸዋለች፤ ሻማ ለኩሳለች።

የድሉን አበባ እያሸተተች፣ ጀግኖች በነሰነሱት የነጻነት ጉዝጓዝ በክብር አዚማለች። ኢትዮጵያ የአፍሪካ – የጥቁር ሕዝቦች ከፍታ ችቦ ለኳሽ!…

አዘጋጅ : ውብሸት ካሳሁን