በአድዋ አባቶቻችን የተቀዳጁት ድል በኛ ሥነ ልቦና ላይ አዎንታዊ የሆነ የሞራል ልዕልና ያጎናፀፈ ነው – የኮንታ ዞን አመያ ከተማ ነዋሪዎች

በአድዋ አባቶቻችን የተቀዳጁት ድል በኛ ሥነ ልቦና ላይ አዎንታዊ የሆነ የሞራል ልዕልና ያጎናፀፈ ነው – የኮንታ ዞን አመያ ከተማ ነዋሪዎች

ሀዋሳ፡ የካቲት 23/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በአድዋ አባቶቻችን የተቀዳጁት ድል በኛ ሥነ ልቦና ላይ አዎንታዊ የሆነ የሞራል ልዕልና ያጎናፀፈ ነው ሲሉ በደቡብ ምዕራብ አትዮጵያ ህዝቦች ክልል የኮንታ ዞን አመያ ከተማ ነዋሪዎች ገልፀዋል።

የአድዋ ድል አገራችን ኢትዮጵያ ከውጭ ወራሪ ለመታደግ አባቶቻችን የህይወት ዋጋ በመክፈል ለሌሎች ነፃነትን ያተረፉበትና ዛሬ በነፃነት የሚንኖርባት ኢትዮጵያን ለኛ የሰጡበት ድል ነው ሲሉ ከአመያ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወ/ሮ ገነት መርሻ፣ አቶ አያለው ከበደና ንጋቱ ኬሃሞ ተናግረዋል፡፡

የአሁኑ ትውልድም ይሔንን የአባቶችን ፈለግ በመከተል የአገር ሠላምና ደህንነት በማስጠበቁ ረገድ ጠንክረው መሥራት እንዳለበት የጠቆሙት ሲሆን በሌሎች ዘርፎችም እንዲህ መሰል ድሎችን በማስመዘገብ ከተቻለ እንደሀገር በአፍሪካ ብሎም በአለም የድል አድራጊነት ማሳያ እንሆናለን ሲሉም ነዋሪዎቹ ገልፀዋል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳደሪ አቶ ነጋ አበራ በበከሉላቸው የአድዋ ድል አባቶቻችን ነፃነታቸውን ለማስከበር የህይወት መሰዋዕትነት በመክፈል በገራ ጉዳይ ላይ በአንድነት በመቆም የማይሸነፍ የሚመስል የነበረውን ሀይል አሸንፈው ያሳዩበት ድል በመሆኑ በኛ ሥነ ልቦና ላይ አዎንታዊ የሞራል ልዕልናን ያጎናፀፈ ሲሉ አሰረድተዋል፡፡

ስለሆነም እኛም እንደ ትውልድ አገራችንን በአስተሳሰብም ሆነ በኢኮኖሚ ሀይል ከቅኝ ግዛት ውስጥ ለማስገባት የሚፈልጉ ሀይሎችንና አስተሳሰቦችንም በመለየት፣ ከአባቶቻችን በተማርነው መሰረት በመተባበርና አንድነታችንም በማጠናከር የአገራችን ሠላምና ደህንነትን በማስጠበቅ በእድገትም ቢሆን በተመሳሳይ ከሌሎች ጋር ዛሬ ላይ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚያስፈልግ አቶ ነጋ አብራርተዋል፡፡ 

ዘጋቢ፡ ብርሃኑ ግንበቶ – ከዋካ ጣቢያችን