የዓድዋን ድል ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታና ሠላም ተመሳሌነት ማዋል ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ፌደሬሽን ም/ቤት ዋና አፈጉባኤ አዳማ ትንጳኤ

የዓድዋን ድል ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታና ሠላም ተመሳሌነት ማዋል ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ፌደሬሽን ም/ቤት ዋና አፈጉባኤ አዳማ ትንጳኤ

ሀዋሳ፡ የካቲት 23/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የዓድዋን ድል ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታና ሠላም ተመሳሌነት ማዋል ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ፌደሬሽን ም/ቤት ዋና አፈጉባኤ አዳማ ትንጳኤ ተናገሩ።

128ኛው የዓድዋ ክበረ በዓል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ ተክብሮ ውሏል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ፌደሬሽን ም/ቤት ዋና አፈጉባኤ አዳማ ትንጳኤ በበኩላቸው የዓድዋ ድል ቀደመት አባቶቻችን ከመላው የሀገሪቱ ጫፍ በስሜትና በወኔ ተጠራርተው የሀገርን ነፃነት በደማቸው ያፀኑበት በመሆኑ ትምህርት የምንወስድበት ነው ብለዋል።

የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን የአሸናፊነትና የፅናት ተምሳሌት መሆኑን ተከትሎ የዛሬው ትውልድ በታሪክ ተወቃሽ ከሚያደርጉ ተግባራት በመላቀቅ የሀገሪቱን ደህንነትና አንድነቷን ማስጠበቅ ይገባልም ብለዋል አቶ አዳማ።

የዓድዋ ድል ከአፍሪካዊነቱ በዘለለ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለውና ቅኝ ገዥዎችን አንገት ያስደፋ መሆኑን የተናገሩት የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ለኢትዮጵያውያን ኩራትና የአይበገሬነት ተምሳሌት መሆኑንም አንስተዋል።

በመሆኑም የአሁኑ ትውልድ ከአድዋ ድል የሚማራቸው በርካታ ጉዳዮች ስለመኖራቸው ያስታወሱት ዶ/ር ዳምጠው ሀገርን ከገባችበት መከራና ፈተና ማላቀቅ ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

ሀገሪቱ አሁን ካለችበት ድህነትና ኃላ ቀርነት ለመላቀቅ ግብግብ ይዛለች ያሉት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወ/ሪት ፍሬህይወት ዱባለ ናቸው።

ኢትዮጵያ ዜጎቿ በአንድነት የሰሯት በጥረታቸው ነፃነቷን አስጠብቀው ለትውልድ ያቆዩ መሆኑን ወጣቱ ትውልድ ሊረዳ ይገባል ያሉት ወ/ሪት ፍሬህይወት ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታና ለሁለንተናዊ ሠላም የድራሻችንን ልንወጣ ይገባልም ብለዋል።

በ128ኛ የዝክረ ዓድዋ በዓል ላይ ዕለቱን የሚያስታውሱ የኪነጥበብ ሥራዎችና ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ዘጋቢ፡ በኃይሉ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን