የአሁኑ ትውልድ ከአድዋ ድል በመማር የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተመላከተ
ሀዋሳ፡ የካቲት 22/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአሁኑ ትውልድ ከአድዋ ድል በመማር ገዥ ትርክቶችን በማፅናት፣ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተውና አንድነቱን ይበልጥ በማጠናከር በሀገሪቱ፣ ሰላም፣ ልማትና ዕድገት እንዲረጋገጥ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አሳስቧል።
የዘንድሮው 128ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በዞኑ በእምድብር ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል።
ኢትዮጵያውያን በሀገር ሉዓላዊነት እና ነጻነት ላይ እንደማይደራደሩ በተግባር ያሳዩበት የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ዘንድሮ ለ128ኛ ጊዜ በመላ ሀገሪቱ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የጉራጌ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ክብሩ ፈቀደ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ የአድዋ ድል የነፃነትና የእኩልነት መሠረት እንዲሁም የጥቁር ህዝቦች ድል መሆኑን በመግለፅ ድሉ የሀገራችን ኩራት የአብሮነታችን፣ የወንድማማችነትና የእህትማማችነት ማሳያና ማስተማሪያ ትልቁ ድላችን ነው።
በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው የአድዋ ዜሮ ዜሮ ፕሮጀክት የወል እውነት፣ የአብሮነትና የገዢ ትርክት ማሳያ ተቋም መሆኑን ጠቁመው ሁሉም ዜጋ በሀገሩ ጉዳይ የማይደራደር እና ጠላትን አንገት የሚያስደፋ መሆኑን እንደሚያመላክት ነው የያስረዱት።
የአሁኑ ትውልድ ታሪክ ነጋሪ ብቻ ሳይሆን ታሪክ ሰሪ ሊሆን እንደሚገባ ያስገነዘቡት አቶ ክብሩ ከአድዋ ድል በመማር ገዥ ትርክቶችን በማፅናት እና ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተውና አንድነቱን ይበልጥ በማጠናከር በሀገሪቱ፣ ሰላም፣ ልማትና ዕድገት እንዲረጋገጥ ለሁለንተናዊ ብልጽግና ሊተጋ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የእምድብር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ግምባሩ በርጋ በበኩላቸው በዓሉ የአድዋ ድል መታሰቢያ ፕሮጀክት በተመረቀበትና ሀገሪቱ ከሶማሊላንድ ጋር የባህር በር የውል ስምምነት በተደረሰበት ማግስት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
በዓሉ ቀደምት አባቶቻችን ለሀገሪቱ ሉአላዊነት፣ ለህዝቦች ነፃነት ሲሉ ከሀገሪቱ ከአራቱም ማዕዘናት በአንድነት ተሰባስበው በዱር በገደሉ ከጠላት ጋር በመፋለም ድል የተቀዳጁበት በዓል ስለመሆኑም አብራርተዋል።
በመሆኑም ጀግኖች አባቶቾቻን የፈፀሙትን የጀግንነት ተግባር ወንድማማችነትና እህትማማችነትን ይበልጥ በማጠናከር ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ብልጽግና ሁሉም በተሰማራበት የስራ ዘርፍ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አመላክተዋል።
ካነጋገርናቸው የዝግጅቱ ተሳታፊዎች መካከል ተማሪ ለምለም ሃይሌ፣ የምስራች ሰይፉና አቶ ምንተስኖት ታምሩ በሰጡት አስተያየት፤ የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊን በአንድነት ለሀገራቸው ነፃነት ከሁሉም አቅጣጫ ወደ ጦር ሜዳ በመትመም መስዋዕትነት በመክፈል ጠላትን ድል የነሱበት የጥቁሮች ኩራት መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ህብረተሰቡ በተለይም ወጣቱ ከአድዋ ድል በመማር አንድነቱን በማጠናከር በሀገሪቱ ሰላምና ልማት እንዲሰፍን የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ገልፀዋል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ ከዞን፣ ከከተማና ወረዳ የተውጣጡ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች፣ መምህራን፣ ተማሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፡ መሀመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ