የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር መልዕክት
“ታላቁ የዓድዋ ድል ቀደምት ኢትዮጵያዊያን የማንነት ክብራቸውን ያስጠበቁበት፣ በብዝኀነታቸው ውስጥ አንድ የወል እውነት የከተቡበት፣ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦችም ፋና ወጊ ሆኖ ለነጻነታቸው እንዲዋደቁ ወኔ የሰነቁበት የሁሉም መጀመሪያ ነው፡፡”
ለመላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንኳን ለ128ኛው የዓድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ።
ኢትዮጵያን ለማንበርከክ የውጭ ወራሪ ኃይሎች በተለያዩ ዘመናት መለስ ቀለስ እያሉ ሲተነኳኩሷት የነበሩ ቢሆንም ጀግኖች አባቶቻችን ጠላትን እንዳመጣጡ እየመከቱ በመመለስ አገራችንን ከቅኝ ተገዥነት ለማዳን በቅተዋል።
ፋሺስት ጣሊያን ከሌሎች ወራሪ ኃይሎች ከፍ ባለአደረጃጀት እና እቅድ ግዛታችንን ሰብሮ በመግባት ግልጽ ወረራ ፈጽሞብናል፡፡ ይህን የተመለከቱት የኢትዮጵያ ሕዝቦች የመሪያቸውን አፄ ሚኒሊክ ጥሪ ተቀብለው ቀፎው እንደተነካበት ንብ ከሁሉም የአገራችን ጫፍ በኅብረት በመትመም የጠላትን ኃይል ዓድዋ ላይ ድባቅ በመምታት ድልን ተቀዳጅተዋል፡፡
የቅኝ ገዥዎችንም ሕልም እስከ ወዲያኛው እንዲጨናገፍ አድርገዋል፡፡ ይህ ድል የመላው ጥቁር ህዝቦች ድል ሆኖም እንዲታወስ አድርገዋል፡፡
የዓድዋ ድል የአብሮነት ሱታፌ ውጤት ነው፤ ኅብረት ገኖ የታየበት፣ መሪና ተመሪ የተናበቡበትና ከእኔነት ይልቅ እኛነት ተዳምረውና ተጋምደው ኃያል ክንድ የፈጠሩበት አውድ ነው፡፡ አብሮነት፣ መናበብና አንድነት ሲደመሩ ወኔን፣ ጉልበትንና ጥበብን ይፈጥራሉ፤ ከሚታለመው ግብ ለመድረስም ጉዞን ያፋጥናሉ፡፡ እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጀመርነውን ሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞ ከግቡ ለማድረስ አብሮነትና የጋራ ርእይ ሊኖረን ይገባል የምንለው ከአድዋ በዙ ስለምንማር ነው፡፡
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ እንደሀገር በዓለም አደባባይ ስሟ ገኖ እንዲታይ የሆነበት፣ ኢትዮጵያዊነትም ለኢትዮጵያዊያን የክብር መጠሪያና በባርነት ለሚማቅቁ ጥቁር ሕዝቦች ደግሞ ስንቅና ትጥቅ ሆኖ ለነጻነታቸው እንዲታገሉ ወኔ የሰነቁበት የሁሉም መጀመሪያ ነው፡፡
የዓድዋ ድል ከሌሎች ድሎች ሁሉ ልቆ ታሪኩ ሳይደበዝዝ ዘመናትን እየተሻገረ የመቀጠሉ ምስጢር የአይቻልምን መንፈስ በመስበር «የሰው ልጅን» እኩልነት በዓለም አደባባይ የመሰከረ በመሆኑ ነው፡፡ የነጮች የበላይነት ያደረ እውነት «Universal Truth» ተደርጎ በሚታመንበት በዚያ የጨለማ ዘመን የዓድዋ ድል አዲስ እውነትን ያዘለች ፀሐይ በሰንሰለታማው የዓድዋ ተራሮች አናት ላይ ወለል ብላ እንድትወጣ ሆናለች፡፡ ጨለማን በብርሐን የገሰሰች፣ ሀሰትን ለእውነት ያስገበረች፣ የበላይነትን ክፉ እሳቤ ሰብራ እኩልነትን ያነበረች የአይበገሬነት ፀሐይ በአደዋ ላይ ለመላው ዓለም ወጥታ ታይታለች፡፡
የዓድዋ ድል የተነጣይነትን ስሜት የገደለ፣ የወል እውነትንና አብሮነትን በጽኑ መሠረት ላይ ያኖረ፣ በዘመናዊው ዓለም የጸረ ቅኝ ግዛት ትግል ነጮች በጥቁሮች ላይ የነበራቸውን የኃያልነት እና በተለምዶ እውነት የሚመስለውን የነጭ የበላይነት የሀሰት ትርክት በእውነተኛው የእኩልነት ትርክት የቀየረ የዓለም ጉልህ የታሪክ ክስተት ነው፡፡
የዓድዋ ድል በኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ ላለፉት 128 ዓመታት የማይዳሰስ ሀውልት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይህ የማይዳሰስ ሐውልት ከ128 ዓመታት በለውጡ መንግሥት ሕያው ሆኗል፡፡ የዘንድሮው የዓድዋ ድል በዓል ድምጽ አውጥቶ የራሱን የተሰነደ ታሪክ የሚናገር ታሪካዊ ሙዚዬም ተገንብቶ በተመረቀበት ማግስት የሚከበር በመሆኑ የተለየ ያደርገዋል፡፡
ሙዚዬሙ የዛሬው ትውልድ የተገነባበትን የታሪክ፣ የባህልና የማንነት ድርና ማግ እንዲገነዘብ፣ በተሰነዱ ታሪኮች ላይ በላቀ ደረጃ በመመራመር ለመላው ዓለም እንዲያስተዋውቅ የራሱን አበርክቶ ለማሳረፍ እድል ይፈጥራል፡፡
የዓድዋ ድል በዓል የኅብረብሔራዊት ኢትዮጵያ ዘመን የማያደበዝዘው በዓል በመሆኑ የዓድዋ ታሪክ በተሰነደ መልኩ ከትውልድ ወደትውልድ እንዲተላለፍ ታሪኩን በሚመጥን ደረጃ በአፍሪካ መዲና በሆነቸው አዲስ አበባ ሙዚዬም መገንባቱ ትውልዱ ከአባቶቹ ታሪክ ተምሮ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት በመገንባት የራሱን ታሪክ እንዲያስመዘግብ ያስችለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከአድዋ ድል ሕዝባዊ ፍቅርን፣ ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን፣ ተምረን ሁሉም ዜጋ በነጻነት የሚኖርባት፣ የበለጸገች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት የበኩላችሁን አስተዋጽኦ የማበርከት ስራችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ከአደራ ጭምር መልእክቴን አስተላልፋለሁ፡፡
የዓድዋን የድል በዓል ስናከብር በእኩልነት፣ በአብሮነት፣ በፍቅርና በመተሳሰብ ሊሆን ይገባል።
በድጋሚ ለመላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንኳን ለ128ኛው የዓድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ።
አገኘሁ ተሻገር
የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ