ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለ128ኛው የአድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለ128ኛው የአድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ሀዋሳ፡የካቲት 22/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለ128ኛው የአድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

“እንኳን ከ128ኛው የዐድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ፡፡”

እናቶቻችንና አባቶቻችን ታላቁን የዐድዋ ድል ከሰጡን 128 ዓመታት አስቆጥረናል፡፡ የዐድዋ ድል የሰጠንን ዕሴቶች ግን በሚገባ የተጠቀምንባቸው አይመስለኝም፡፡ ቢያንስ አራቱን ታላላቅ የዐድዋ ድል ዕሴቶች ለሀገር ግንባታ ልንጠቀምባቸው የግድ ይለናል፡፡

የመጀመሪያው ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ነው፡፡ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የኢትዮጵያ ዋናው መልኳ መሆኑን ከዐድዋ ዘመቻ በተሻለ ለማሳየት የቻለ ክሥተት በዘመናዊ ታሪካችን አናገኝም፡፡ የዐድዋ ዘመቻ ሁለት ጊዜ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን አሳይቷል፡፡

የመጀመሪያው በጦርነቱ ዘመቻና ድል ጊዜ ነው፡፡ ዛሬ በምናውቃት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ማኅበረሰቦች መካከል ወደ ዐድዋ ያልዘመተ ወገን የለም ብሎ መናገር እውነትን መናገር ነው፡፡ ሁለተኛው ክሥተት ደግሞ የዐድዋ ድል በተገኘ በሰባት ዓመቱ የዐድዋ በዓል ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ሲከበር ትርዒቱን ያቀረቡት ከተለያዩ የሀገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦችች የመጡ የኢትዮጵያ ጦር አባላት ነበሩ፡፡ በዚህ ትርዒት ኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊት ሀገር መሆንዋን በዐደባባይ ሰልፈኛው አሳይቶ ነበር፡፡

ይሄንን በዐድዋ ዘመቻና በዓል የተንጸባረቀ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት አጽንተን ልንይዘው ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ማለት ኅብረ ብሔራዊ ማነነት ያላቸው ሕዝቦች በአንድነት የሚኖሩባት ሀገር ናት፡፡ ኅብረ ብሔራዊነታቸው ከፈጣሪ ሲያገኙት ነው፡፡ አንድነታቸውን ደግሞ እነርሱ ራሳቸው በዘመናት ትሥሥርና መሥዋዕትነት ገንብተውታል፡፡ ኢትዮጵያ እነዚህ ሁለቱን፣ ነገር ግን አንዱ ከሌላው ጋር ሳይነጣጠል የሚኖሩትን መገለጫዎቿን ትታ ኢትዮጵያ አትሆንም፡፡ በእያንዳንዱ ጉዞዋ ይሄንን እያረጋገጠች መጓዝ አለባት፡፡

ሁለተኛው ዕሴት ለታላቅ ሀገራዊ ዓላማ ሲባል ንኡስ ፍላጎቶችን መሠዋት ነው፡፡ ወደ ዐድዋ የዘመቱ ሁሉ በወቅቱ በነበረው ሥርዓተ መንግሥት የሚስማሙና የተደሰቱ አልነበሩም፡፡ አንዳንዶቹ እንዲያውም ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ግጭትም ቅራኔም ነበራቸው፡፡ አንዳንዶቹም በነበረው ሀገራዊ ሁኔታ ቅር ተሰኝተው ከጠላት ጋር የሚሠሩ ነበሩ፡፡ ነገሩ የሀገር ጉዳይ ሲሆንባቸው ግን ሁሉም ንኡስ ፍላጎቶቻቸውን ትተው፣ ለታላቁ ፍላጎት ለሀገር ህልውና መሥዋዕት ለመሆን መጡ፡፡ ማንኛውም ፍላጎት ከሀገር ፍላጎት በታች መሆኑንም አሳዩን፡፡

እንኳን ዛሬ ብዙ ዓይነት መረጃ፣ ዕውቀትና የሐሳብ መንገዶች ባሉበት ዘመን ቀርቶ ከመቶ ዓመት በፊትም ሰዎች ልዩ ልዩ ፍላጎቶች ነበሯቸው፡፡ በፍላጎቶቻቸው የተነሣም ቅራኔዎችና ግጭቶች ነበሩ፡፡ ሁሉንም ለአንድ ዓላማ የምታስተሣሥር ዓላማ ሀገር የምትባለው ናት፡፡ ዛሬም ንኡስ ፍላጎቶቻችን ከኢትዮጵያ አይበልጡም፡፡

ኢትዮጵያን የሚያዳክም፣ የሚያሳንስና የሚያሳጣ መንገድ ከትልቁ ዓላማ የሚጋጭ መንገድ ነው፡፡ ጦርነት የትልቁ ዓላማ የኢትዮጵያ ህልውና ማስከበሪያ እንጂ የንኡስ አካባቢያዊና ግላዊ ዓላማዎች ማስፈጸሚያ ሊሆን አይገባም፡፡ ጦርነት ለትንሽ ነገር የሚወጣ ወጪ አይደለም፡፡

ዘመኑ ብዙ ፈተናዎች እንዳሉት ሁሉ ብዙ የመፍትሔ አማራጮችም አሉት፡፡ መከራከር፣ መነጋገር፣ መወያየት፣ በሕግ መዳኘት፣ አንዱ ሌላው መሸከም፣ የትየለሌ አትራፊ መንገዶች አሉት፡፡ ትልቋ ዓላማ ኢትዮጵያን ለማበልጸግ ስንል ንኡስ ዓላማዎቻችንን እያመሙን እንኳን ቢሆን መሠዋት አለብን፡፡

ሦስተኛው ዕሴት የጦርነትን ምርቅና ፍትፍት ማወቅ ነው፡፡ ጦርነት ምንም ያህል በአሸናፊነት ቢጠናቀቅ የሚያስከፍለው ዋጋ አለው፡፡ የዐድዋ ዘማቾች ሀገር ሆኖባቸው፤ ሉዓላዊነት ሆኖባቸው፤ የታላቅ ዓላማ ጉዳይ ሆኖባቸው እንጂ ጦርነት የመጀመሪያ አማራጫቸው አልነበረም፡፡ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ነገሩ በሰላም እንዲቋጭ ደጋግመው ጽፈዋል፤ ለምነዋል፡፡

አልሆነም፡፡ የዐድዋ ዘመቻ በኢትዮጵያ አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ የኢትዮጵያ ዘማቾች ግን ከድል የተመለሱት በደስታ ብቻ አይደለም፡፡ ከፊታውራሪ ገበየሁ ጀምሮ አያሌ ጀግኖች ለትልቁ ዓላማ ለኢትዮጵያ ህልውና ሲሉ ተሠዉተዋል፡፡ የሄዱት ሁሉ አልተመለሱም፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት በድልና በኀዘን ነው የተመለሰው፡፡ ብዙዎችም በየአካባቢያቸው በፌሽታ አልነበረም ድሉን ያከበሩት፡፡ እንኳን በራሳቸው ወገኖች፣ በጣልያኖች መሞት ኢትዮጵያውያን አዝነዋል፡፡

ጦርነት ተገድደን ብቻ ለትልቁ ዓላማ ስንል የምንገባበት የመጨረሻ አማራጭ እንጂ ከደረት ኪሳችን ቶሎ የምንመዘው አይደለም፡፡ እዚህም እዚያም የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በጠመንጃ ለመፍታት መነሣት የዐድዋ ዘማቾችን ኀዘን አለመጋራት ነው፡፡ የዐድዋ ዘማቾች ድልን ብቻ ሳይሆን ጦርነት የሚያስከትለውን መከራም ጭምር አስተምረውን አልፈዋል፡፡

አራተኛው ትዕግሥት፣ ዝግጅት እንጂ ፍርሐት አለመሆኑን ነው፡፡ ጣልያኖች ከሦስት ዓመታት በላይ ኢትዮጵያን ሲገፏት ነበር፡፡ በሀገሪቱ የደረሰውን የእንስሳትና የሰዎች ማለቅ ምክንያት አድርገው ትንኮሳውን አባብሰው ነበር፡፡ ኢትዮጵያ እየተገፋች እንኳን ቢሆን ታግሣለች፡፡ ትዕግሥቷ ግን ከዐቅመ ደካማነቷ የመጣ አይደለም፡፡ ለባሰው ነገር

እየተዘጋጀች ስለነበር እንጂ፡፡ እህል እስኪደርስ፣ ሰው እስኪያገገም፤ የተገዛው መሣሪያ እስኪደርስ፣ የደረሰው መሣሪያ ከጦሩ ጋር እስኪላመድ ታግሣለች፡፡ በመጨረሻ ግን የትዕግሥቷን ውጤት በዐድዋ ተራሮች ላይ አሳይታለች፡፡

ኢትዮጵያ ዛሬም ትታገሣለች፡፡ እየተገፋችም እንኳን ቢሆን ትታገሣለች፡፡ የምትታገሠው ስለሚያቅታት አይደለም፡፡ ለባሰው ነገር ስለምትዘጋጅ ነው፡፡ ያ የባሰው ነገር ሲመጣ የዐደዋውን ድል በብዙ እጥፍ ትደግመዋለች፡፡

እነዚህን ዕሴቶች ዘወትር ማሰብ፣ አስበን መተግበር እንድንችል የሚያስታውሰን ነገር ያስፈልግ ነበር፡፡ ዐድዋን የሚመጥን ታሪኩንም ዕሴቱንም የምናስብበት መታሰቢያ ዘመቻው በተጀመረበት ሥፍራ ባስገነባን ማግሥት ነው በዓሉን የምናከብረው፡፡

ይሄም ለዘንድሮው በዓል ሞገስና ክብር ጨምሮለታል፡፡ ዛሬ መታሰቢያውን በከበረ ሁኔታ አከናውነናል፡፡ ነገ ግን የአድዋን ዕሴቶች በሚገባ በመጠቀም እንደ ዐድዋ ተራሮች የጸናች ኢትዮጵያን መገንባት ይቀረናል፡፡ ያ ደግሞ የሁላችንንም ስክነት፣ ብስለትና ጥምረት ይፈልጋል፡፡

በድጋሚ መልካም የዐድዋ ድል በዓል ይሁን፡፡

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

የካቲት 22/2016 ዓ.ም