ያልተዘመረላቸው ጀግና ፊታውራሪ ጌጃ ገርቦ ማንናቸው
በአራቱም ማዕዘናት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እስከ ህይወት መስዋዕትነት ድረስ ወድ ዋጋ የከፈሉ እልፍ ጀግኖች ያፈራች ማህፀነ ለምለም ሀገር ናት፤ ኢትዮጵያ ።
ፊታውራሪ ጌጃ ገርቦ በአሁኑ መጠሪያ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከሀዲያ ብሔር አብራክ የተገኙ በአመካ ወረዳ ሊቅቦ ተብሎ በሚጠራበት የተወለዱ የሀገር ባለውለታ የአድዋ ጀግና ናቸው፡፡
ፊት አውራሪ ጌጃ በአደዋ ዘመቻ የአጤ ምኒልክን ጥሪ ተቀብለው ከሀዲያና ከምባታ አከባቢዎች ወደ 5ሺ ጦር እየመሩ በአድዋ ጦርነት በፊት አውራሪነት ከዘመቱ ጀግኖች መካከል አንዱ ናቸው፡፡
”የሐበሻ ጀብዱ የተደበቀው ማስታወሻ” ላይ እንደሰፈረው ፊት አውራሪ ጌጃ ገሪቦ በአድዋ እና በማይጨው የፀረ ፋሺስት ዘመቻ ላይም ትልቅ ሚና የነበራቸው ያልተዘመረላቸው ጀግና ናቸው ።
በ1888 ዓ.ም በአድዋ ጦርነት፣ በ1928 ዓ.ም ጣሊያን የቀድሞውን የአድዋ ሽንፈት ለመቀልበስ ኢትዮጲያን ድጋሚ በወረራት ወቅትም ፊት አውራሪ ጌጃ የሀዲያን ጦር እየመሩ ዘምተዋል፡፡
ፊት አውራሪ ጌጃ ገርቦ በዚህ መልክ የሀዲያን ጦር እየመሩ የአድዋ ጉዞ እስከሚጀመር ጦራቸውን አሰልፈው በአዲስ አበባ በጊዜያዊነት አርፈው ነበር፡፡
አዲስ አበባ ገብተው ጉዞ ወደ አድዋ ጉዞ እስኪጀመር ድረስ በጊዚያዊነት ያረፉበት አካባቢም ‹‹የጌጃ ጦር›› ሰፈር ይባል ስለነበር ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ይህ አከባቢ ”ጌጃ” ሰፈር በመባል ይታወቃል፡፡
”ጌጃ” ማለት የሀዲይኛ ቃል ሲሆን፤ ትርጓሜውም ጠብቆ ሲነበብ ትልቅ፣ የከበረ፣ ወፍራም የሚል አቻ ትርጉም አለው ።
አላልተን ያነበብነው እንደሆን ደግሞ ደቦ፣ በጋራ መስራት፣ መተጋገዝ እንደማለት ነው። ፊት አውራሪ ጌጃ በተንቤን ግንባር በአውሮፕላን ቦምብ ጥቃት እንደተሰው ይነገራል ።
የአድዋና የማይጨውን ጦርነት ስለመሩት ጀግና ፊታውራሪ ጌጃ በበቂ ሁኔታ ባለመፃፉ እና የኢትዮጵያ ታሪክ ማስታወሻዎች ውስጥ ተመዝግቦ ባለመዘከሩ በአግባቡ እንኳ በመጽሐፍ የተሰነዱ ፅሁፎችን ማግኘት አዳጋች ሲሆን ይስተዋላል።
በመሆኑም ”የበሉበትን ወጭት ሰባሪ” እንዲሉ የዚህ ሀገር ባለውለታ ፊታውራሪ ገድል በተወጡት ሚና ልክ ገድላቸው ሲዘከር፣ ጀግናውንም የሚመጥን ጥናትና ምርምር ሲደረግ አይታይምና ሊታሰብበት ይገባል ።
አዘጋጅ፦ ሄኖስ ካሳ -ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ