የአሁኑ ትውልድ ጀግኖች አባቶቻችን በአድዋ ጦርነት ወቅት የፈፀሙትን አኩሪ ድል እንደ መስፈንጠሪያ በመጠቀም በአንድነት በሰላም እና በልማት ሥራዎች ላይ ሊደግም እንደሚገባ ተገለፀ
ሀዋሳ፡ የካቲት 20/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአሁኑ ትውልድ ጀግኖች አባቶቻችን በአድዋ ጦርነት ወቅት የፈፀሙትን አኩሪ ድል እንደ መስፈንጠሪያ በመጠቀም በአንድነት በሰላም እና በልማት ሥራዎች ላይ ሊደግም እንደሚገባ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪው አብዱ ሙባሪክ ተናገሩ፡፡
ኢትዮጵያውያን አንገታቸውን ለሰይፍ ደረታቸውን ለጥይት በመስጠት በሀገር ሉዓላዊነት እና ነጻነት ላይ እንደማይደራደሩ ያስመሰከሩበት አንጸባራቂው የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ዘንድሮ ለ128ኛ ጊዜ በመላ ሀገሪቱ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል።
በበዓሉ ዙሪያ ከደሬቴድ ጋር ቆይታ ያደረጉት የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ አብዱ ሙባሪክ እንደገለፁት፤ አድዋ እንደ ሰንሰለት የተያያዘ የድል ሽግግር እንጂ አንድ ቦታ ብቻ በአንድ ጊዜ የተፈጸመ አይደለም፡፡
ወራሪ ቡድኖቹ ወደ አፍሪካ ሲመጡ የሀሰት ስምምነትና ማግባባትን በመጠቀም የመውረር ዓላማን ይዘው እንደገቡ ጠቅሰው በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር የተካሄደው ጦርነት ዋነኛው መንስኤም የውጫሌ ስምምነት አንቀጽ 17 እንደሆነም በማሳያነት አንስተዋል።
በመሆኑም ህዝቡ አዲሱ ትውልድ ጀግኖች አባቶቻችን በአድዋ ጦርነት ወቅት የፈፀሙትን አኩሪ ድል እንደ መስፈንጠሪያ በመጠቀም በአንድነት በሀገር ሰላም እና ልማት ሥራዎች ላይ ሊደግመው እንደሚገባ ተናግረዋል።
በጦርነቱ መላው ኢትዮጵያውያን የዘር፣ የፆታ፣ የቀለም፣ የሃይማኖትና የፖለቲካ ልዩነት ሳይበግራቸው ከየአቅጣጫው በመሰባሰብ አሻራቸውን ማሳረፋቸውን ተናግረው ድሉም የቀደመው ትውልድ ከሁሉም አቅጣጫ ተንቀሳቅሶ ዋጋ የከፈለበት የብሄራዊ ኩራት፣ የመተባበርና የመደማመጥ ውጤት መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ታዲያ ይህ በከፍተኛ ገድል የተገኘው የአድዋ ድል ጥቁር በነጭ ላይ የተቀዳጀው ድል ከመሆኑም በላይ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለቅኝ ግዛት እጅ ባለመስጠት ማንነቷን በጽኑ ጠብቃ እንድታቆይ ያስቻለ ብሎም በአለም አቀፍ ማህበረሰብ በተለይም በአውሮፓወያን ዘንድ ጎልታ እንድትታይ ዕድል የፈጠረ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።
ስለሆነም የተገኘው ድል ለኢትዮጵያውያን ብሎም ለአፍሪካዊያን ትልቅ ኩራት እንደሆነም ምሁሩ አመላክተዋል፡፡
የአድዋ ድል በኢትዮጵያውያን ብሎም በአፍሪካውያን ዘንድ ብሔራዊ ስሜት እንዲፈጠር በማድረግ የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ እንዲጀመርና ለጥቁር ህዝቦች ወንድማማችነት መፈጠር እንዲሁም በአዲስ አበባ የበርካታ ኤምባሲዎች መከፈት ምክንያት በመሆን ትልቅ ሚና መጫወቱንም ምሁሩ አውስተዋል።
የአድዋ ድል መታሰቢያ ፕሮጀት በአዲስ አበባ ተገንብቶ መመረቁ የቀደምቱ ትውልድ አንድነትን በመፍጠር ባደረገው ተጋድሎ ነፃነቷን የጠበቀች ሀገር ስለማስረከቡ ዕውቅና መስጠት እንደሆነ ያስረዱት ምሁሩ ይህም አዲሱ ትውልድ ታሪክን በማስታወስ ያለውን ግንዛቤ ይበልጥ በማሳደግ በሀገር ሰላም፣ አንድነት፣ ልማትና ዕድገት ላይ የድርሻውን እንዲወጣ መነሳሳትን እንደሚፈጥርም አስታውቀዋል።
ዘጋቢ፡ መሀመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ