የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2016 በጀት ዓመት የመስተዳድር ምክር ቤትን የ6 ወር እቅድ አፈጻጸም በሙሉ ድምጽ አጸደቀ
ሀዋሳ፡ የካቲት 19/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎ የመስተዳድር ምክር ቤቱን የበጀት አመት የ6 ወር አፈጻጸም ገምግሞ፥ ጠንካራና ደካማ ያላቸውን ነጥቦች ለይቶ የማሰተካከያ ሃሳብ አክሎበት አጽድቋል።
በ6ኛ ዙር 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ በቀረበው ሪፖርት መነሻ፥ ከምክር ቤት አባላት ለቀረበው ሃሳብና አስተያየት ምላሽና ማብራሪያ የሠጡት የመስተዳድር ምክር ቤት አባላት፥ መስተካከል ያለባቸውን ጉድለቶች በማረም፣ የተነሱ በጎ ሃሳቦችን በቀጣይ በግብዓትነት ተጠቅመው እንደሚሰሩ አስረድተዋል።
ከንጹሕ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ፣ ከደሞዝ ክፍያ መዘግየት፣ ከገቢ አሰባሰብና አስተዳደር ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች፣ የአፈር ማዳበሪያ ስርጭትና ተደራሽነት ህጋዊ ስርዓቱን ጠብቆ እንዲመራ ማድረግ፣ ከዩራፕ የገጠር መንገድ ግንባታና የመንገድ ጥገና ጋር ተያይዞ ለተነሱ ችግሮች የመስተዳድር ምክር ቤት አባላት ምላሽና መፍትሔዎችን አመላክተዋል።
ከግብርና፣ ከትምህርት፣ ከጤና፣ ከመልካም አስተዳደር፣ ከሠላምና ጸጥታ፣ ከከተማ መሠረተ ልማትና ከመብራት ጋር ተያይዞ ለቀረበው ሃሳብ ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ድጋፍ ርብርብ እንደሚሻ ተጠቁሟል።
ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሻው ጣሰው ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተነሱ ሃሳቦች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፥ የሠላምና ጸጥታ ጉዳይ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫን አድርገን መስራት በመቻላን በሌሎች ሴክተሮች ለተመዘገበው ውጤት ማጠንጠኛ መሆኑን አስረድተዋል።
ክልሉ በአዲስ መልኩ የመደራጀቱን ያክል ያለበትን የበጀት እዳ፣ የሰው ኃይል እጥረት፣ የሎጂስቲክስ ቁሳቁስ አሉታዊ ጫናዎች ተቋቁሞ የክልሉን ህዝብ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የተሔደበትን ርቀት አሳይተዋል። በዚህም ተስፋ ሰጪና ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ተችሏል ብለዋል።
በቀጣይም ምክር ቤቱ አስፈፃሚ አካላትን ደግፎና አግዞ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንዲቻል እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎ የመስተዳድር ምክር ቤቱን የ2016 በጀት አመት የ6 ወር አፈጻጸም በሙሉ ድምፅ ተቀብሎ በመጽደቅ የዛሬ ውሎ አጠናቋል።
ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ
More Stories
በከተሞች የሚስተዋሉትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ሰፊ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ
ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ በመምራት እና በመጠቀም የአካባቢን ገጽታ መገንባት እንደሚገባ ተጠቆመ
የአዳሪ ትምህርት ቤቶች መስፋፋት ጥራት ያለው ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት እንደሚያስችል ተገለጸ