ዛሬ አመሻሽ በሊግ ካፕ ቼልሲ እና ሊቨርፑል ለዋንጫ ይጫወታሉ
በእንግሊዝ የውስጥ ሊግ የ2023-24 የውድድር ዘመን የመጀመሪያ የፍፃሜ ውድድር በሆነው የሊግ ካፕ ቼልሲ እና ሊቨርፑል በዌምብሌይ ስቴዲየም ይገናኛሉ።
በ21ኛዉ ክፍለ ዘመን ሁለቱ ክለቦች ለ6ኛ ጊዜ በፍፃሜ ውድድር ይጫወታሉ።
ባለፈው የውድድር ዓመትና በዘንድሮው የውድድር ዘመን በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ደካማ የሚባል የውጤት ጎዳና ላይ የሚገኘው ቼልሲ እኤአ በ2022 መጋቢት ወር በአዲሶቹ የክለቡ ባለቤቶች እጅ ከወደቀ በኋላ በወንዶች ዋናው ቡድን የመጀመሪያ የፍፃሜ ጨዋታ ያካሂዳል።
በያዝነው የውድድር ዓመት ለአራትዮሽ ዋንጫ እየተወዳደረ የሚገኘው ሊቨርፑል በዓመቱ የመጀመሪያውን ዋንጫ መደርደሪያው ላይ ለማስቀመጥ ይፋለማል።
በቼልሲ ቤት በመጀመሪያ ዓመት ቆይታቸው በሊግ ካፕ ለፍፃሜ የደረሱት ማውሪዚዮ ፖቸቲኖ በእንግሊዝ ምድር ሁለተኛ የሊግ ካፕ የፍፃሜ ውድድራቸውን ያከናውናሉ።
ከዚህ ቀደም እኤአ በ2015 የቶትንሃም አሰልጣኝ ሆነው ለፍፃሜ ቢደርሱም በቼልሲ መረታታቸው አይዘነጋም።
9 ጊዜ የሊግ ካፕ ዋንጫን በማንሳት ቀዳሚ የሆኑት ሊቨርፑሎች ከክለቡ ጋር ከ8 ዓመታት ቆይታ በኋላ በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ለሚለያዩት አሰልጣኝ ዩርገን ክሎፕ መጨረሻቸውን ለማሳመር የሞት ሽረታቸውን እንደሚያደርጉ ተጠብቋል።
የሊቨርፑል አሰልጣኝ ሆነው የመጀመሪያ የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታቸውን ካከናወኑት አሰልጣኝ ማዉሪዚዮ ፖቸቲኖ (ቶትንሃም ሳሉ) ጋር በመርሲሳይድ በመጨረሻ ዓመት ቆይታቸው በፍፃሜ መገናኘታቸው ብዙዎችን አስገርሟል።
ለቼልሲ ዋንጫ ማንሳት፣ በሊጉ ይዘው የሚያጠናቅቁት ደረጃ በቀጣይ ዓመት የአውሮፓ ተሳታፊ የማያደርጋቸው ከሆነ በአቋራጭ የይሮፓ ሊግ ተሳታፊ ያደርጋቸዋል።
ከዚህ ቀደም ቼልሲ እና ሊቨርፑል በሊግ ካፕ ፍፃሜ ሁለት ጊዜ ተገናኝተዋል።እኤአ በ2005 እና በ2022 ነው የተገናኙት።
በ2005 ቼልሲ በጆዜ ሞሪኒዮ እየተመራ የራፋ ቤኒቴዙን ሊቨርፑል 3ለ2 አሸንፎ ዋንጫ አንስቷል።
ከሁለት ዓመት በፊት ሊቨርፑል በመለያ ምት አሸንፎ ዋንጫ ማንሳቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነዉ።
በውድድር ዓመቱ የሊቨርፑልን ያኽል ብዙ ጎል ያስቆጠረ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ክለብ የለም። የመርሲሳይዱ ክለብ በሁሉም ውድድሮች 67 ጎሎችን አስቆጥሯል።
5 የተለያዩ ተጫዋቾች 10 እና ከዛ በላይ ጎል ያስቆጠሩለት ብቸኛው ክለብ ነው ከ5ቱ ታላላቅ ሊጎች።
ሞሃመድ ሳላህ (19) ዲያጎ ጆታ (14) ዳርዊን ኑኔዝ (13) ኮዲ ሃክፖ (11) ሉይዝ ዲያዝ (10) ጎሎችን በሁሉም ውድድሮች ለሊቨርፑል አስቆጥረዋል።
በአንፃሩ የቼልሲ 5ቱ የፊት መስመር ተጫዋቾች በድምሩ 37 ጎሎችን ነው ያስቆጠሩት።
አመሻሽ 12 ሰዓት በለንደን ዌምብሌይ ስቴዲየም በሚጀምረው ጨዋታ በቼልሲ በኩል ቤን ቺልዌል እና ክርስቶፈር ንኩንኩ ለጨዋታው ዝግጁ ሲሆኑ ቲያጎ ሲልቫ ለጨዋታው መድረሱ አጠራጣሪ ሆኗል።
በርካታ ቁልፍ ተጫዋቾች ጉዳት ያስተናዱበት ሊቨርፑል ሞሃመድ ሳላህ፣ ዳርዊን ኑኔዝ እና ዶሚኒክ ዦቦዥ ላይ ለጨዋታው ሊደርሱ እንደሚችሉ ተነግሯል።
በሙሉቀን ባሳ
More Stories
ሮድሪጎ ቤንታንኩር ከእግር ኳስ ጨዋታዎች ታገደ
በቀቤና ልዩ ወረዳ የብልጽግና ፓርቲ 5ተኛ አመት ምስረታን ምክንያት በማድረግ ማህበረሰብ አቀፍ የማስ ስፖርት በወልቂጤ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል
የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ባህሉ ያደረገ ጤናማና ንቁ ማህበረሰብ ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ