የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የእስካሁን አፈፃፀም እና ባጋጠሙ ተግዳሮቶች ዙሪያ የንቅናቄ መድረክ እያካሄደ ነው
ሀዋሳ፡ የካቲት 07/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ከሁሉም የአስተዳደር እርከን ፋይናንስ መዋቅሮች ጋር የ2018 በጀት ዓመት የእስካሁን አፈፃፀም እና ባጋጠሙ ተግዳሮቶች ዙሪያ የንቅናቄ መድረክ በዱራሜ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አረጋ እሸቱ ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከባለፉት ዓመታት ጀምሮ የማንሰራራት ዘመን በማወጅ ማንሰራራቷን የሚያረጋግጡ ግዙፍ ሜጋ ፕሮጀክቶችን እየገነባች ትገኛለች ያሉ ሲሆን በክልሉም በተለያዩ ዘርፎች ተጨባጭ ውጤት ማምጣት ችሏል ብለዋል።
ለፕሮጀክቶቹ በፍጥነት መጠናቀቅ የፋይናንስ ሴክተር ትልቁን ድርሻ ይወስዳል ያሉት ዋና አስተዳዳሪ፤ ያለውን ውስን ሀብት በአግባቡ በማስተዳደር የሚያጋጥሙ ብልሹ አሰራሮችን በማረም እና በዕቅድ በመምራት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዘይቱና ኢብራሂም፤ ክልሉ በአዲስ መልክ እንደመዋቀሩ የነበሩ ዕዳዎችን በማቃለል የአሰራር ክፍተቶችን በመቅረፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከዕዳ ነፃ ክልል ለመፍጠር በተሰራው ስራ ወደ አዲስ ምዕራፍ ማሻገር ተችሏል ብለዋል።
የነበሩ ተግዳሮቶችን በመቅረፍ በክልሉ የነበሩ ዕዳዎችን 80 ከመቶ መክፈል እንደተቻለ የተናገሩት ወ/ሮ ዘይቱና፤ ለዚህም በየደረጃው ካሉ ተቋማት ጋር በትብብር መሰራቱን አንስተዋል።
በክልሉ የሀብት አስተዳደር ስርዓት በጠንካራ መስረት ላይ በማስቀመጥ ንብረቶች በምን መልኩ እየተመሩ መሆናቸውን መገምገምና የታዩ ክፍተቶችን መቅረፍ የመድረኩ ዓላማ ነው ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ የዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች የፋይናንስ ተቋማት የስራ አፈፃፀም ክንውን ሪፖርት ቀርቧል።
ዘጋቢ፡ ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በህብረተሰብ ተሳትፎ እየተከናወኑ የሚገኙ የመንገድ ልማት ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ገለፀ
የሲዳማ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ
የተማሪዎች ውጤትና ስነ-ምግባርን በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት አለባቸው – የቀቤና ልዩ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት