በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በህብረተሰብ ተሳትፎ እየተከናወኑ የሚገኙ የመንገድ ልማት ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ገለፀ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በህብረተሰብ ተሳትፎ እየተከናወኑ የሚገኙ የመንገድ ልማት ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ገለፀ

ቢሮው የ2018 በጀት አመት የ6 ወራት የህብረተሰብ ተሳትፎ ስራዎች አፈፃፀምና የገጠር መንገዶች ትስስር እና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም አፈፃፀም ግምገማ መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።

”በህብረተሰብ ተሳትፎ የተሳለጠ የመንገድ ልማት” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው በዚሁ መድረክ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ሀላፊ መሀመድ ኑርዬ(ዶ/ር)፤ የመንገድ ልማትን ጨምሮ በተለያዩ የመሰረተ ልማት ስራዎች ላይ የህብረተሰቡ ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን ገልፀዋል።

የዜጎችን ልማት ለማረጋገጥ የራስን አቅም መጠቀም ወሳኝ ነው ያሉት ሀላፊው፤ በዚህም በትምህርት፣ በመንገድና በሌሎችም ዘርፎች ውጤታማ ተግባራትን ማከናወን ተችሏል ብለዋል።

በክልሉ በህብረተሰብ ተሳትፎ የሚሰሩ የመንገድ መሰረተ ልማቶችን ይበልጥ ለማሳደግ በተጠናከረ መልኩ መስራት ከሁሉም ባለድርሻ አካል ይጠበቃል ሲሉም አሳስበዋል ዶ/ር መሀመድ።

በተለይም በገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና (RCFSP) ፕሮግራም የተከናወኑ ተግባራት አበራታች ቢሆኑም በአፈፃፀም ዙሪያ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በቀጣይ መቅረፍ እንደሚገባም አመላክተዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የጉራጌ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ የህያ ሱልጣን፤ በዞኑ ባለፉት 6 ወራት በመንግሥትና በህብረተሰቡ ትብብር 479 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱንና አሁን ላይ የእቅዱን 70 በመቶ ማሳካት መቻሉን ጠቁመዋል። የግማሽ አመቱ የመንገድ ግንባታም 60 በመቶ መድረሱን በማከል።

የስልጤ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ ከዲር አብደላ በበኩላቸው፤ በዞኑ በመንገድ ልማት ዘርፍ ማህበረሰቡ ጠንካራ ተሳትፎ በማድረግ ላይ መሆኑንና በዞኑ 480 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመገንባት ታቅዶ እየተሰራ የሚገኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በሀዲያ ዞን የሚሻ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አለማየሁ ኤርዲዶም፤ ህዝቡ ቀደም ካለው ጊዜ በተለየ መልኩ በተነቃቃ ሁኔታ የመንገድ ልማት ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ዘጋቢ፡ ሙባረክ አክመል – ከወልቂጤ ጣቢያችን