በተለያዩ የልማት ዘርፎች አበረታች ተግባራት መከናወናቸውንና ተጠናክሮ አንዲቀጥል የሁሉንም ቁርጠኝነት የሚጠይቅ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ም/ቤት አስታወቀ

ሀዋሳ፡ የካቲት 14/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በተለያዩ የልማት ዘርፎች አበረታች ተግባራት መከናወናቸውንና ተጠናክሮ አንዲቀጥል የሁሉንም ቁርጠኝነት የሚጠይቅ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ም/ቤት አስታውቋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ከወከላቸው ህዝብ ጋር ለመወያየት የሚያስችል የምክክር መድረክ አርባ ምንጭ ከተማ ላይ አካሂደዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፀሀይ ወራሳ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ፍላጎት ለማሳካት በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸው በገጠር ልማት፣ በግብርናና በማህበራዊ ዘርፍ አበረታች ለውጦች መመዝገባቸውን ተመልክተናል ብለዋል።

በክልሉ ተጀምረው ያላለቁ በርካታ የመሠረተ ልማቶችና የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው የሚፈልጉ ወጣቶች መኖራቸውን የገለጹት አፈ ጉባኤዋ እነዚህንና ሌሎች ተግባራትን በአግባቡ ለማከናወን ከህዝቡና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በተለይም የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላትም ከወከላቸው ህዝብ ጋር በአመት ሁለት ጊዜ በሚደረግ ውይይት በመገናኘት የህዝቡን የመልማት ጥያቄ በየደረጃው መመለሱን ማረጋገጣቸው ተገቢ እንደሆነ አንስተዋል።

በኢፌዲሪ ህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ መለሰ መና እንዳሉት፤ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በተሰጠው ሀላፊነት መሠረት አባላት በአመት ሁለት ጊዜ ከወከላቸው ህዝብ ጋር በመገናኘት በአከባቢያቸው የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ነቅሶ በማውጣት ምላሽ እንዲሰጥበት በመከታተል ላይ መሆኑ ይታወቃል።

በምልከታቸውም የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን መለየትና በመልካም አስተዳደር ረገድ የሚታየው ውስንነት በይበልጥ እንዲቀረፍ ትኩረት መሠጠት እንዳለበትም አንስተዋል።

ልዩ ድጋፍ ለሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች ትኩረት መደረጉን መከታተል እንደሚያስፈልግና አስፈጻሚ አካላትና ም/ቤቶች በቅንጅት የህዝብ ጥያቄ ባለቤት የሚያገኝበትና ተቋማትም ለተጠየቁ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡበት ሊሆን ይገባልም ብለዋል አቶ መለሠ።

የሰላም ግንባታ፣ የግብርና ልማት፣ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴና የግብር አሰባሰቡ ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ መከናወኑን መከታተል እንደሚገባ ጠቁመው የንግዱን ስርአት ጤናማነት ማረጋገጥና የጸረ ሙስና ትግሉን ማቀጣጠል እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች እንደገለጹት፤ የህዝብ ተወካዮች እንደመሆናችን ከህዝቡ የሚነሱ አስፈላጊ የሆኑ የልማት ጥያቄዎችን ነቅሶ በማውጣት በየደረጃው እንዲመለሱ ለአስፈጻሚው አካል ማቅረብና መከታተል ያስፈልጋል።

በተለይም አስፈጻሚው አካል የህዝቡን ጥያቄ ለመለየትና ለመመለስ እንዲያስችል ከህዝብ ተወካዩ ጋር የጋራ መድረክ መፈጠር አለበት ብለዋል።

የህዝቡን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ እንዲያስችል በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ም/ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ወላይቴ ቢቶ የህዝብ ተመራጮች ከአስፈጻሚው አካል ጋር በቀጣይ በቅንጅት ልንሰራ ይገባል ብለዋል።

ከተወያዮች ለተሰነዘሩት ጥያቄዎች ከመድረክ ምላሽ የተሰጠ ሲሆን ከዚህ ቀደም ተነስተው ምላሽ የተሰጠባቸውን ማሳወቅና አዳዲስ ጥያቄዎችን በአግባቡ መያዝና ለአስፈጻሚው ማቅረብ ይገባል ተብሏል።

ዘጋቢ፡ ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን