ሀዋሳ፡ የካቲት 14/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ህዝብና መንግስትን በማቀራረብ የመንግስትን የልማት ስራዎች ለማሳለጥ የብዙኃን መገናኛ ሚናቸው የጎላ መሆኑ ተገልጿል።
የሀዲያ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ የ2016 አጋማሽ የስራ ዘመን አፈፃፀም ግምገማና የቀጣይ አቅጣጫዎች ዕቅድ ዙሪያ የጋራ መወያያ መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሄዷል።
የሀዲያ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ታደሰ ዘርፉ በዞናዊ፣ ክልላዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማነሳሳት በመረጃ የበለፀገ ዜጋን ከመፍጠር ባለፈ የሀገሪቱን መልካም ገጽታ ከማጎልበት አንጻር ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።
በመንግስት የመረጃ ልውውጥ ተግዳሮት የሚሆኑ ጉዳዮችን በመለየት በትኩረት እንደሚሰራ የጠቆሙት አቶ ሳሙኤል በተለያዩ ማህበራዊ ሚድያዎች የህብረተሰቡን ጥላቻ የሚያበረታቱ፣ ሀገርን የሚበትኑና ልማትን የሚያስተጓጉሉ መረጃዎችን ከመመከት አንጻር የመንግስት ሚዲያዎች ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው አመላክተዋል።
በመድረኩ የተገኙት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አምሪያ ሲራጅ እንደገለፁት፤ በክልሉም ሆነ በሀገር ደረጃ የታሰቡ የመንግስት የልማት ዕቅዶችን ከግብ ለማድረስ የብዙኃን መገናኛ ትልቅ ድርሻ አላቸው።
ብዙኃን መገናኛ ህዝብና መንግስትን በማቀራረብ የመንግስትን የልማት ስራዎች ያሳልጣል ያሉት ኃላፊዋ የተግባቦት ክፍተቶች ከተፈጠሩ ግን አለመግባባቶችን ከመፍጠርም በላይ ሀገርን የማፍረስ አቅም ያላቸው እንደመሆኑ ዘርፉ በከፍተኛ ጥንቃቄ፥ በኃላፊነት ሊመራ የሚገባ መሆኑን አመላክተዋል።
በመንግስት የሚሰሩ የልማት ተግባራትን በብዙኃን መገናኛ ስራዎች ማስደገፍ መረጃዎችን ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ ለተሻለ ውጤታማ ስራ እንደሚያነሳሳ ጠቁመው የሚድያ ጠቀሜታንና አስፈላጊነት የተረዳ አመራር መፍጠር ደግሞ በጋራ ተግባቦት የልማት ስራዎችን ለማሳለጥ ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።
የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም መጫ በበኩላቸው ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ሽግግር ብዙኃን መገናኛ ትልቅ ድርሻ አላቸው ብለዋል።
በተለያዩ ሀሰተኛ ሚዲያዎች መረጃ ውሸት የበለይነትን በያዘ በዚህ ወቅት የመንግስት ሚዲያዎች ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው በመጠቆም።
በሚዲያ የፈረሱ ሀገራት እንዳሉ ሁሉ የሀገራትን አንድነት ከማጎልበት አንጻርም ብዙኃን መገናኛ ጉልህ ሚና እንዳላቸው የጠቆሙት አቶ አብርሃም የሚዲያን 4ኛ መንግስትነት ሚና በአግባቡ በመጠቀም የመወሰንና የማስወሰን አቅም አላቸው ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የተግባቦት ስራዎች የመንግስትን የልማት ተግባራት የሚያሳልጡ እንደመሆናቸው የጋራ ግንዛቤ በመያዝ ተዓማኒ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በሚደረጉ ጥረቶች የድርሻቸውን እንደሚወጡ አመላክተዋል።
በመድረኩም በሴክተሩ በአጋማሽ ዓመቱ የተከናወኑ ተግባራት ሪፖርት ቀርቦ በመገምገም ከታችኛው መዋቅር አካላት ጭምር በቀጣይ ስራዎች ዙሪያ የግብ ስምምነት በመፈራረም በጋራ ተግባቦት ወደ ስራ የሚገባበት አቅጣጫ ላይ የጋራ ውይይት ተካሄዷል።
ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ