በዞኑ ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሚገኝ የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ
ሀዋሳ፡ የካቲት 14/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዞኑ ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሚገኝ የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ አስታውቋል፡፡
መምሪያው ከወልቂጤ ፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጅ እና ሳተላይት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ለቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት በወልቂጤ ከተማ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ሀላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ እንደገለፁት፤ መምሪያው ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተለይም በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ለተሰማሩ አካላት የመከታተል፣ የመገምገም፣ ግንዛቤ የመፍጠርና የመመዘን ስራ ይሰራል፡፡
የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ እንደ ሀገር ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት እንደሚገኝና በጉራጌ ዞንም መነቃቀቱን ገልፀው የማህበረሰቡ ባህልና ማንነት በሚገልፅ መልኩ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ስልጠናው በምግብ አዘጋጃጀት፣ በምግብ ጥራት፣ በንፅህና አጠባበቅና በቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ላይ ትኩረት ያደረገ እንደነበር ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅም በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የትምህርት ክፍል ከፍቶ ከማስተማር ጎን ለጎን ስልጠናዎችን በመስጠት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ወ/ሮ መሰረት አመልክተዋል፡፡
የወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅና ሳተላይት ኢንስቲትዩት ዲን አቶ ኸይሩ አህመዲን በበኩላቸው ኮሌጁ በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለማስወገድ ታሳቢ ያደረጉ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝና ከእነዚህም መካከል የሰለጠነ የሰው ሀይል መምረት ዋነኛ አላማው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ስልጠናው በሆቴል ቱሪዝም ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ያለመ መሆኑና እንደሀገር በትኩረት እየተሰራበት የሚገኘውን ይህ ዘርፍ የጉራጌ ዞንም የተሻለ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
በዘርፉ ወውጤታማ ስራዎችን ለማከናወን አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ የሚስተዋሉ ጉድለቶችን ለመቅረፍ ሁሉም አካላት በባለቤትነት ሊሰሩ እንደሚገባና ሰልጣኞች በስልጠናው ያገኙትን እውቀት ተግባር ላይ ማዋል እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
በጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ የቱሪዝም አገልግሎት ብቃት ማረጋገጥ ቡድን መሪ የሆኑት ወ/ሮ ወይንሸት ሰተቶ በሰጡት አስተያየት ስልጠናው በዋናነት ያተኮረው በሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት ተቋማት ላይ መሆኑና በእነዚህ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት ማሻሻል ላይ ያለመ ነበር ብለዋል፡፡
የሆቴልና ቱሪዝም ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓታቸውን ለማሻሻል ለሰራተኞቻቸው አስፈላጊውን ግንዛቤ በመስጠት ከፅዳት ጀምሮ ለተጠቃሚዎች አስፈላጊውን እንክብካቤ በመስጠት ተቋማቱ ገቢያቸውም ጭምር ለማሳደግ እንሚረዳቸው አመላክተዋል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ስልጠናው በሆቴሎችና ቱሪዝም ተቋማት ከዚህ በፊት በልምድ የሚከናወኑ ተግባራት ወደ ሙያ የሚቀይርና ዘርፉን እንደሚያነቃቃ አውስተዋል፡፡
በስልጠናው ያገኙት እውቀት ተግባር ላይ በማዋል ሆቴሎችና ቱሪዝም ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን እንደሚሰሩ አስረድተዋል፡፡
በመድረኩ ከዞን፣ ከወረዳ፣ ከከተማ አስተዳደሮች፣ ከወልቂጤ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅና የሆቴል ባለቤቶች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ መላኩ ንማኒ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ