የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች የሚያስከብሩ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎች ተከናውነዋል
በ37ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች የሚያስከብሩ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎች መከናወናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዶክተር መለስ ዓለም በሳምንታዊ መግለጫቸው፣ ከአፍሪካ ሕብረት መሪዎች ጉባኤ በተጓዳኝ ከሀገራት ጋር ውጤታማ የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያጠናክሩ ውይይቶች መደረጋቸውን እንስተዋል።
ከጉባኤው ጎን ለጎን ከአንጎላ፣ ከደቡብ አፍሪካ ጋር የተፈረሙ ስምምነቶች ትልቅ ስኬት መሆናቸውን ጠቅሰው፥ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ወደከፍታ እየወጣ የታየበት ሳምንት ነበር ብለዋል።
ታሪካዊ ወዳጅነት ካላት ዝምባብዌ ጋር ውጤታማ ምክክር መደረጉን ገልፀው፣ በግብርና እና ሌሎችም መስኮች በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ ስለመደረሱ ገልፀዋል።
በሌላ በኩል እንደቤተሰብ የሚተያይ ህዝብ ያላቸው ኢትዮጵያና ኬንያ የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ መካሄዱን ጠቅሰው፥ ሁለቱ ሀገራት በሰባት ዘርፎች ስምምነት ማድረጋቸውን ነው የጠቀሱት።
ስምምነቱም በቱሪዝም፣ ባህልና ስፖርት፣ በዱር እንስሳት ጥበቃ፣ በአሳ ልማት፣ ፔትሮሊየም እና በማረሚያ ቤት አገልግሎት፣ እና በሲቪል ሰርቪስ አቅም ግንባታ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ነው ማለታቸውን ኢዜአ በዘገባው ገልጿል።
የቪዛ ጉዳይ ሌላው ስምምነት መሆኑን ጠቅሰው፣ በ1958 ጀምሮ የተደረገው የቪዛ ነፃ ስምምነት በኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት መልኩ እንዲሆን መከለሱን ነው ያነሱት።
ይህም ለዘመናት የነበረውን ወዳጅነት ይበልጥ ወደላቀ ደረጃ እንደሚያሳድግ ገልፀዋል።
የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት በመንግስት ለውጥ የማይዋዥቅ እንደሆነ ገልፀው፣ ወዳጅነታቸው በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ነው ብለዋል።
ከሌሎችም የአፍሪካ ሀገሮች ጋር በተደረገ ውይይት ሀገራቱ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት እንዲፀና ፍላጎት ማሳየታቸውንና ኤምባሲያቸውን ለማጠናከር መወሰናቸውን ገልፀዋል።

More Stories
የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና የ2019 ጠቋሚ ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው
የጠምባሮ ልዩ ወረዳ አርሶ አደሮች የመኸር እርሻ የማሳ ዝግጅት ቢያደርጉም በቂ ግብዓት አለማግኘታቸውን ገለጹ
ፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ የህዝብና የመንግስት አገልግሎቶችን የሚያፋጥን በመሆኑ ለሁሉም ለማድረስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ