በክልሉ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲጠበቁ ሁሉም የሚጠበቅበትን ሊወጣ ይገባል – አቶ አክመል አህመዲን

በክልሉ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲጠበቁ ሁሉም የሚጠበቅበትን ሊወጣ ይገባል – አቶ አክመል አህመዲን

ሀዋሳ: የካቲት 14/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በክልሉ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተጠብቀው የህግ የበላይነት ይረጋገጥ ዘንድ ሁሉም የሚጠበቅበትን ሊወጣ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ አክመል አህመዲን አሳሰቡ::

የክልሉ ፍትህ ቢሮ የስድስት ወራት የሥራ ክንውኑን በየደረጃው ከሚገኙ የዘርፉ መዋቅርና ባለድርሻ አካላት ጋር በቡታጅራ ከተማ እየገመገመ ይገኛል::

ባለፉት ስድስት ወራት ቢሮው የክልሉን ህዝብ ጥቅም የማስጠበቅ፣ የህብረተሰቡን ንቃተ ህግ የማሳደግ፣ ወንጀል ፈጻሚዎች ለህግ እንዲቀርቡ እና ተጠያቂ እንዲሆኑ ማስቻሉን የግምገማ መድረኩን በንግግር የከፈቱት የቢሮው ኃላፊ አቶ አክመል አህመዲን ገልጸዋል::

ከቢሮው እስከታችኛው መዋቅር ድረስ በተለወጠ አመለካከትና አሰራር አገልግሎት አሰጣጡን ውጤታማ ለማድረግ የተሠራው ሥራ የተሟላ ባይሆንም አበረታች ውጤት ታይቶበታል ብለዋል::

በወንጀልና በፍትሀብሔር፣ በህግ ጥናት ማርቀቅና ማስረፅ፣ በሙስና ወንጀሎች፣ በጠበቆችና ሲቪክ ማህበራት ክትትል፣ በወንጀል ጉዳዮች፣ በክስ ዝግጅትና በችሎት ክርክር ከማዕከል እስከ ታችኛው መዋቅር በግማሽ አመቱ ወደተያዘው ግብ መድረስ የሚያስችል አፈፃፀም ተመዝግቧል::

የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል በክልሉ መልካም አስተዳደር ማስፈንና ከህዝብ የሚነሱ እሮሮዎችን ለመቀነስ በጅምር ላይ ያለ ተግባር ቢኖርም በቀጣይ ልዩ ጥረትና ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል::

መድረኩ በተመዘገቡ ውጤቶች ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ ወቅቱ የሚጠይቀውንና የህዝባችንን አዳጊ ፍላጎት ማዕከል በማድረግ ክፍተቶቻችንን ለይተን ለተሻለ አፈፃፀም ለማምጣት በሚያስችል መልኩ ውይይት የሚደረግበት ነው ብለዋል::

በክልሉ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተጠብቀው የህግ የበላይነት ይረጋገጥ ዘንድ ሁሉም የሚጠበቅበትን ሊወጣ እንደሚገባም ነው አቶ አክመል ያሳሰቡት::

በግምገማ መድረኩ የፍትህ ዘርፍ ተጠሪ ተቋማት አመራሮች እና የክልል፣ የዞንና ልዩ ወረዳ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል::

ዘጋቢ፡ ማሬ ቃጦ