በመረጃ የበለፀገ ህብረተሰብን በመፍጠር በጋራ ተግባቦት ብልጽግናን እሙን የማድረግ ተግባር ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑ ተገለፀ

በመረጃ የበለፀገ ህብረተሰብን በመፍጠር በጋራ ተግባቦት ብልጽግናን እሙን የማድረግ ተግባር ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ የካቲት 14/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በመረጃ የበለፀገ ህብረተሰብን በመፍጠር በጋራ ተግባቦት ብልጽግናን እሙን የማድረግ ተግባር ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑ ተገልጿል።

የሀዲያ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ የ2016 አጋማሽ የስራ ዘመን አፈፃፀም ግምገማና የቀጣይ አቅጣጫዎች ዕቅድ ዙሪያ የጋራ መወያያ መድረክ በሆሳዕና ከተማ እያካሄደ ይገኛል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀዲያ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ታደሰ በመክፈቻ ንግግራቸው ወቅት እንደገለፁት፤ ለማናቸውም የመንግስት ስራዎች ስኬት  የጋራ ተግባቦት ቅድሚያ የሚሰጠው ነው።

ይልቁንም በዚህ ወቅት የጋራ ብልጽግናን እሙን ለማድረግ የዘርፉ ተግባራት ትልቅ ትኩረት የሚሹ ናቸው ብለዋል።

አቶ ሳሙኤል አክለውም ዘርፉ በዞናዊ፣ ክልላዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማነሳሳት በመረጃ የበለፀገ ዜጋን ከመፍጠር ባለፈ የሀገሪቱን መልካም ገጽታ ከማጎልበት አንጻር ሚናው የጎላ ነውም ብለዋል።

በመድረኩ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አምሪያ ሲራጅ እና የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም መጫን ጨምሮ የዞን እና የተለያዩ የመንግስት መዋቅሮች ባለድርሻ አካላትና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

በአጋማሽ ዓመቱ የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገም ከታችኛው መዋቅር አካላት ጭምር በቀጣይ ስራዎች ዙሪያ የግብ ስምምነት በመፈራረም በጋራ ተግባቦት ወደ ስራ የሚገባበት አቅጣጫ ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን