በየአካባቢው በትናንሽ ምክንያቶች የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በሰከነ ሁኔታ በንግግር የመፍታት ልምድ ሊዳብር እንደሚገባ በአሪ ዞን የሰሜን አሪ ወረዳ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና የጎሳ መሪዎች አሳሰቡ

በየአካባቢው በትናንሽ ምክንያቶች የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በሰከነ ሁኔታ በንግግር የመፍታት ልምድ ሊዳብር እንደሚገባ በአሪ ዞን የሰሜን አሪ ወረዳ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና የጎሳ መሪዎች አሳሰቡ

በሰሜን አሪ ወረዳ ራፂ እና አርፋሮ አካባቢ በመሠረተ ልማት ጥያቄ መነሻ ተፈጥሮ የነበረን አለመግባባት በዕርቀ ሠላም መጨረስ የሚያስችል የህዝብ ኮንፈረንስ መድረክ በተካሄደበት ወቅት ነው ይህንን ያሳሰቡት።

የአካባቢው ማህበረሰብ በዋናነት የመብራት፣ የመንገድና መሰል የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ብናቀርብም ምላሽ አላገኘንም በሚል ሁከት አስነስተው አለመግባባት ተፈጥሮ የተለያዩ ግለሰቦች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር በኮንፈረንሱ የተሳተፉ የአካባቢው ነዋሪዎች አንስተዋል።

ጥያቄዎችን በሰከነ መልኩ በመነጋገር ምላሽ ማግኘት የሚያስችል ሠላማዊ አማራጭ ሳለ በአልተፈለገ መልኩ ህገ ወጥ እንቅስቃሴ በማድረግ ሁከት የፈጠሩ ከህዝቡ መካከል መኖራቸውን የመድረኩ ተሳታፊዎች ገልፀው እነዚህ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

እነዚህ አካላት ሠላም ወዳድ የሆነው ህዝብ ከወረዳ አመራር ጋር ጥርጣሬ እንዲኖር እንዳደረጉም የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች አንስተው እንቅስቃሴያቸው ስህተት በመሆኑ ዕውነተኛ ይቅርታ ልብ ኖሯቸው ዳግም በመሰል ድርጊት ላይ እንዳይሳተፉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በተለይ በአካባቢው ላይ የሚነሳውን የመብራት ጥያቄ መንግስት በተቻለ መጠን መመለስ አለበት ያሉት ነዋሪዎቹ፤ ለዚህም ከራሳቸው የሚጠበቅባቸውን ድርሻ እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

ማንኛውም የልማት ጥያቄ በሰከነ መልኩ የመነጋገር ልምድ ሊዳብር እንደሚገባ ያሳሰቡት በመድረኩ የተገኙት የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና የጎሳ መሪዎች ከዚህ ውጭ ለአካባቢው ብቻ ሳይሆን እንደሀገር የሚጠቅም አይደለም ብለዋል።

መንግስትም በየጊዜው ከህዝቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ቃል እየገባ ጊዜ ወስዶ በልማት ጠያቂው ህዝቡ በኩል ቁጣ በማያስነሳ መልኩ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመድረኩ የተገኙት የአሪ ዞን ፖሊስ መመሪያ ሀላፊ ኮማንደር ሽኩን አርቲ በየትኛውም መልክ ልማታዊ ጥያቄዎችን በሠላማዊ መንገድ ጠይቆ ምላሽ ከማግኘት ውጭ ያልተገባ እንቅስቃሴ ፈፅሞ አይጠበቅም ብለዋል።

በራፂና አርፋሮ አካባቢ የመብራት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በተሳሳተ መልኩ እንቅስቃሴ ያደረጉ 11 ግለሰቦች ተጠርጥረው በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ቢሆንም በአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች፣ በሀይማኖት አባቶችና በጎሳ መሪዎች ግሳጽ በይቅርታ በዕርቀ ሠላም ጉዳያቸው እንዲፈታ በመድረኩ ተደርጓል።

የሰሜን አሪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገረመው ኃይለማርያም እና የወረዳው የመንግስት ዋና ተጠሪና ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ እልፍዮስ ባድሜ በጋራ እንደገለፁት በራፂና አርፋሮ በመብራት ጥያቄ መነሻ ያልተገባ እንቅስቃሴ መደረጉ ፈፅሞ ስህተት ነው።

መንግስት ጥያቄውን ተቀብሎ በክልሉ ስር መሰል ጥያቄዎች ከቀረቡ አካባቢዎች ጋር በማመጣጠን ምላሽ ለመስጠት እየሠራ እንደሚገኝ ገልፀው በሰከነ መልኩ ጥያቄው የአንድ አካባቢ ብቻ ሳይሆን የወረዳ ጥያቄ ጭምር በመሆኑ ከስሜት በፀዳ መልኩ ሊቀርብ ይገባል ብለዋል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ያልተገባ እንቅስቃሴ ውስጥ የተሳተፉ አካላትም ህዝቡን ይቅርታ በመጠየቅ ዳግም በመሰል ድርጊት ላለመሳተፍ ቃል ገብተዋል።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን