ኢትዮጵያውያን ታሪካችንና ባህላችንን ተገንዝበን ለዘላቂ የሰላም ግንባታ የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ፕሬዘዳንት ተናገሩ

ሀዋሳ፡ የካቲት 13/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ኢትዮጵያውያን ታሪካችንና ባህላችንን ተገንዝበን ለዘላቂ ሀገራዊ የሰላም ግንባታ የበኩላችንን መወጣት አለብን ሲሉ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር አህመድ ሙስጠፋ ተናግረዋል።

አድዋ ለዘላቂ ሰላም እና ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ በሚል መርህ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ የአድዋ በአል በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

የአድዋ ድል በአል የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ከሰላም ሚኒስተር ጋር በመተባበር በአሉ በሚዛን ግቢ በተከበረበት ወቅት የዩኒቨርስቲው ፕሬዘዳንት ዶክተር አህመድ ሙስጠፋ እንደተናገሩት፥ አድዋ በሀገር፣ በአህጉርና በአለም አቀፍ ደረጃ አዲስ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ድል የተመዘገበበት የድል ቀን እንጂ ወታደራዊ ድል ብቻ አለመሆኑን ተናግረዋል።

የአድዋ ድል ተጋድሎ መቻቻል፣ አብሮነትንና አንድነትን ያሳየ መገለጫ በመሆኑ ለአሁኑ ትውልድ መደማመጥና በጋራ መቆምን የሚያስተምር ስለሆነ፥ አዲሱ ትውልድ ከአድዋ ድል ትልቅ ትምህርት ሊወስድ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያዊ እሴትን ለመመለስ አንድነትን ለማጠናከር አሁን የተጋረጡብንን ፈተናዎች ለመሻገር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድርሻ ትልቅ በመሆኑ፥ የዩኒቨርስቲ ሙሑራኖችም የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ፕሬዘዳንቱ ተናግረዋል።

የአድዋ ድል አከባበር ላይ የመወያያ ጹሁፍ ካቀረቡት ሙሁራኖች መካከል የታሪክ መምህሩ እጪ ዶክተር አማረ ፋንታሁን እና የማህበረሰብ ሳይንስ መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር ታገል ወንድሙ በበኩላቸው፥ የአድዋ ድል በአል የኢትዮጵያውያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያን እንዲሁም የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ድል መሆኑን ተናግረዋል።

በጦርነቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የተሳተፈበት የድል በአል በመሆኑ በአሁኑ ሰአት በሀገራችን የሚያለያዩን በርካታ ነገሮች ቢኖሩም አንድ የሚያደርጉን በርካታ በመሆናቸው ከአድዋ ትምህርት ወስደን አንድነታችንን ይበልጥ ልናጠናክር ይገባልም ብለዋል።

በዚሁ የሙሁራን ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ፥ ካለፈው ትርክት ወጥተን ለኢትዮጵያ አንድነት በጋራ ልንቆም ይገባልም ብለዋል።

ከዩኒቨርስቲው ተማሪዎች መካከልም ተማሪ ሀሰን በላይ እና ተማሪ ዳዊት ደፋሩ በበከሉቸው አድዋ የጥቁሮችን አንድነት አልሸነፍ ባይነትን ያሳየ መሆኑን አውስተዋል። በተለይም ዩኒቨርስቲዎች የትንሿ ኢትዮጵያ መገለጫ ስፍራ በመሆናቸው አንድነታችንን በማጠናከር ረገድ ተማሪው የራሱን ድርሻ ሊያበረክት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ ከተገኙት ተሳታፊዎች መካከል አቶ ሻንቆ ጋኪናንስ እና አቶ ሰለሞን ኮርችቴት እንዲሁም አቶ ግራዊ የኪ በሰጡት አስተያየት፥ አድዋ የጥቁር ህዝቦችን የነጻነት ቀን የኢትዮጵያውያን ጌጥ በመሆኑ በአድዋ ተምሳሌት ኢትዮጵያዊያን አባቶቻችን ሀገራቸው እንዳቆዩት ሁሉ ዛሬም ያሉትን ልዩነቶችን በማጥበብ ከልዩነት ይልቅ በአንድነት ላይ መስራት ያስፈልጋልም ብለዋል።

ዘጋቢ፡ አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን