ሀዋሳ፡ የካቲት 13/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት በሰላምና ጸጥታው ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትን የሚገመግም የውይይት መድረክ በሆሳዕና ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
በዚህ የውይይት መድረክ የክልላዊ ጸጥታና የሰላም ግንባታ ስራዎች ላይ የልዩ ወረዳዎችና ዞኖች ዋና አስተዳዳሪዎች፣ የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች እና የፖሊስ አዛዦች እየተሳተፉ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው፥ የመድረኩን ዋነኛ አላማ የክልሉን የጸጥታ ሁኔታ በመረዳት ለቀጣይ ጊዜያት ዝግጅት ማድረግ መሆኑን አመላክተዋል።
ክልሉ እንደ አዲስ ተዋቅሮ ስራ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ የነበረው የሰላም ማስከበርና የጸጥታ ስራ እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም፥ አሁንም የጸረ ሰላም ኃይሎችን እንቅስቃሴ ትኩረት ሰጥቶ በንቃት መከታተል ያስፈልጋል ብለዋል።
በሌላ በኩል አጠቃላይ የጸጥታውን መዋቅር ያለበትን ቁመና በመፈተሽ ውስጡን የማጥራት ስራ መስራት እንደሚገባም ርእሰ መስተዳድሩ አንስተዋል።
የጸጥታውን ኃይል ፖሊሳዊ ስነ-ምግባር ማስጠበቅ ላይ እንዲሁም ኑሮውን ለማሻሻል ስራዎች መሰራት ይገባል ብለዋል፡፡
በውይይት መድረኩ የክልሉን ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ በሚመለከት በክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ በአቶ ተመስገን ካሳ መነሻ ጽሁፍ የቀረበ ሲሆን ውይይት ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ዘጋቢ: ወንድወሰን ሽመልስ
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ