የኢፌደሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲቲዩት ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታት በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ፋጣን ለውጥ ለማምጣት ጉልህ ሚና መጫወቱ ተገለፀ

የኢፌደሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲቲዩት ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታት በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ፋጣን ለውጥ ለማምጣት ጉልህ ሚና መጫወቱ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ የካቲት 09/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኢፌደሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲቲዩት ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታት በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ፋጣን ለውጥ ለማምጣት ጉልህ ሚና መጫወቱ ተገልጿል፡፡

ኢንስቲቲዩቱ በተጠናቀቀው ግማሽ ዓመት ያከናወናቸውን ተግባራት የሚገመግም መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ አካሂዷል፡፡

የኢፌደሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲቲዩት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቴክኒክና ሙያ መምህራንና ቴክኒሺያኖችን በቅድመ ምረቃና በድህረ ምረቃ እንዲሁም አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት እያበቃ ዘመናት ተሻግሯል፡፡

የኢንስቲቲውቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩክ ከድር የተቋሙን የግማሽ ዓመት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ መድረክን በንግግር በከፈቱበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ተቋሙ የ2016 በጀት ዓመትን ዓመተ-ልህቀት ብሎ ከጀመረ ወዲህ በጥናትና ምርምር የተለዩትን መፍትሄ እንዲያገኙ በማድረግ ሀገራዊ ሃላፊነቱን ተወጥቷል፡፡

በይበልጥ የሥራ ፈጣሪነትን እሳቤን ወደ ተግባር ለመቀየር በተደረገው ጥረት ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን የተናገሩት ዶ/ር ብሩክ አገራዊ የልማት ፍላጎቶችን የሚያሳኩ ብቁ ዜጎችን ለመፍጠር ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር ጠንካራ ተግባራት መከናወናቸውንም አንስተዋል፡፡

ኢንዱስትሪውን በተለይም የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን ምርትና ምርታማነታቸውን ብሎም ተወዳዳሪነታቸውን የሚያጎለብቱ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ተጨባጭ ስኬት አስመዝግበዋል ብለዋል፡፡

በተቋሙ የቴክኖሎጂና ኢንተርፕራይዝ ልማት ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሪት ፀዳለ ተክሉ የዘርፉን ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ የሰው ኃይል የማፍራትና ምርትና ምርታማነትን የሚያሻሽሉ ቴክኖሎጂዎችን የማቅረብ ተልዕኮ በውጤታማነት መመራቱን አውስተዋል፡፡ 

የኢንስቲቲውት ኢንዱስትሪ ትስስርን በማጎልበት የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል የሚሉት ወ/ሪት ፀዳለ በሀገሪቱና በመላው ዓለም ሠፊ የሰው ኃይል የሚያሳትፈውን የብየዳ ቴክኖሎጂ ክህሎትን አሰልጣኞችና የኢንዱስትሪ ቴክኒሻኖች እንዲያገኙ በማድረግ ብቃታቸውን መሳደግ መቻሉን አንስተዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ከተማ በተገመገመው የኢፌደሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲቲዩት የግማሽ ዓመት የሥራ ክንውን የአስተዳደር፤ የጥናትና ምርምር ማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሁም የቴክኖሎጂና ኢንተርፕራይዝ ልማት ተግባራት ሪፖርት ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ዘጋቢ፡ በኃይሉ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን