ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ ባይሰጣቸውም በጊዜ ሒደት እንደ ችግሮቹ መጠን እልባት ይሰጣል – አቶ አሊ ከድር
ሀዋሳ፡ የካቲት 09/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) “ህብረብሄራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ሃሳብ በወራቤ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው የውይይት መድረክ ላይ የተለያዩ ሃሳብ፣ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተዋል።
ሁሉም ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ ባይሰጣቸውም በጊዜ ሒደት እንደ ችግሮቹ መጠን እልባት ይሰጣል ሲሉ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ከድር ተናግረዋል።
ከልማትና መልካም አስተዳደር አኳያ እንደ ሀገርና ክልል ያሉ መሠረታዊ ለውጦችን ማስቀጠል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በማተኮር፥ ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ክዋኔዎች በመንግሥትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ ሊሰራ ያስፈልጋል ብለዋል።
ከኑሮ ውድነት፣ ከኃይል አቅርቦት፣ ከውኃና እንደ ከተማ አስተዳደር ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በመጠቀምና በማልማት ረገድ፣ እንደ ሀገር በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው የሰላም እጦትና ብልሹ አሰራሮች ሀገርን እያቀጨጩ ናቸውና በጋራ መታገል ይጠይቃል ሲሉም አንስተዋል።
በእነዚህና መሰል ጉዳዮች ላይ ምላሽና ማብራሪያ የተሰጣቸው ሲሆን፥ በዋናነት የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ከድር እንደተናገሩት ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት ነው ሁላችንም ለሰላም ዘብ መቆም ይጠበቅብናል ብለዋል።
በሃሳብና በነጻ የፖለቲካ ምህዳር ላይ የተመሰረተ ሰላምን መፍጠር እንጂ በጉልበትና በአፈሙዝ ችግርን መፍታት እንደማይቻል በማመን ራስን ለውይይትና ድርድር ማዘጋጀት ያስፈልጋል ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።
ሌብነትን ያለ ህብረተሰቡ ተሳፎ ማሸነፍ እንደማይቻል የተናገሩት አቶ አሊ፥ በዚህ ላይ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
የኃይል አቅርቦቱን ችግር ለመፍታት የተለያዩ ስራዎች እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፥ የሙከራ ስራው በሙሉ ሲጠናቀቅ የኃይል አቅርቦት ተደራሽነት በቅርቡ ይረጋገጣል ሲሉም አክለዋል።
ሁሉም ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ ባይሰጣቸውም በጊዜ ሒደት እንደ ችግሮቹ መጠን እልባት ይሰጣል ብለዋል።
የመንገድ መሰረት ልማትና የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ጥያቄዎችም በዚህ አግባብ የሚመለሱ ስለመሆናቸው አረጋግጠዋል።
አብሮነት የህልውና መሰረት ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው አሰባሳቢ ትርክቶች ላይ በስፋት መስራት ይገባልም ብለዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብሬ ጋጌ በበኩላቸው የመንግስት አቅም ህዝብ ነው ህዝብና መንግስት ደግሞ ተደጋግፈው መቀጠል ያለባቸው ናቸው ያሉ ሲሆን እንደ ስማችን ማዕከላዊ አስተሳሰብን ይዘን ልንጓዝ ይገባል ነው ያሉት።
ያለውን ሀብት በአግባቡ እየተጠቀምን አይደለም የሚለው ገዢ ሃሳብ ነው በማለት ቁጭታችንን በመቋጨት ለመልማት መዘጋጀት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ብልጽግና የሚረጋገጠው የህዝብ ተሳትፎ ሲረጋገጥም ነው ብለዋል።
እንደ ክልል ለትምህርት የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ነው ያሉት አቶ ገብሬ፥ ዞኑ ተወዳዳሪ ዜጋን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል እንዳይደለም ነው ያሉት።
የሰላም ችግር የሚመነጨው ባልተገባ መንገድ ስልጣን ለመውሰድ በሚደረግ ጥረት ነው ያሉት ኃላፊው፥ ይህም ለሰላም እጦት ምክንያት እየሆነ የመጣ ስለመሆኑ ጠቁመው፥ ችግር ከመፍጠር ይልቅ በመነጋገር ማመን እንደሚጠብቅም ነው ያሳሰቡት።
ዘጋቢ፡ ብሩክ አማረ
More Stories
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ
የይርጋጨፌ ከተማን የኮሪዴር ልማት ለነዋሪዎች ምቹ ከተማ እንዲትሆን ከማድረግ ባለፈ የከተማዋን ገፅታ የቀየረ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ
የፍትህ ሪፎርም ተግባራዊ በማድረግ በዘርፉ እየታዩ ያሉ ማነቆዎችን ማረም እንደሚገባ ተገለፀ