እንደ ሀገር ያሉ ሀብቶችን በማልማት መበልጸግ እንዲቻል ከመቼውም ጊዜ በላይ በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ የካቲት 08/2016 ዓ.ም (ደረሬቴድ) እንደ ሀገር ያሉ ሀብቶችን በማልማት መበልጸግ እንዲቻል ከመቼውም ጊዜ በላይ በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተጠቁሟል።

ሀብት በመፍጠር በጉዞ ላይ የገጠሙ ችግሮችና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ህዝባዊ የውይይት መድረክ በቴፒ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ ተገኝተው ለታዳሚያን ማብራሪያ የሰጡት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ህዝቦች ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ እንደገለጹት ከህብረተሰቡ የተነሱት ጉዳዮች በየዘርፉ ባሉት ባለድርሻ አካላት የሚፈቱና ወሳኝ ወቅታዊ ሐሳቦች መሆናቸውን በመናገር እንደሀገር ባለፉት ጊዜያት የገጠሙ የሠላም ችግሮች አስፈላጊ ለውጥ እንዳይመዘገብ አድርገዋል ብለዋል።

እንደሀገር በአንዳንድ አካባቢዎች ያለውን የሠላም እጦት በሚመለከት ሀገሪቱ የሰሜኑ ጦርነት በወንበር ዙሪያ ውይይት በማድረግ ሠላም መፍጠር የቻለች በመሆኑ አሁንም በሆደ ሰፊነት በሠላማዊ መንገድ ጉዳዮን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ እዳለ የቢሮ ኃላፊ ተናግረዋል።

በየቦታ እየተፈጠሩ ያሉት ጽንፈኛ ኃይሎች ለህዝብ ሳይሆን የሚሰሩት የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ብሎም ወንድም ወንድሙን እየገደለ በመሆኑ በጋራ መታገል ያስፈልጋል ያሉት የቢሮ ኃላፊው ከመሠረት ልማት ከኑሮ ውድነት ተያያዥ ጥያቄዎችን በዕቅድ በማካተት ከሦስት ወር በኋላ ውጤቱን መልሰን እንገመግማለን ብለዋል።

እንደሀገር ከሚታዩት የሠላም መደፍረሶች ደቡብ ምዕራብ ክልል የተሻለ ሠላም አለው ያሉት ተወያዮች በበኩላቸው በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚታየውን የሠላም መደፍረስ የፌዴራሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ሊፈታው ይገባልም ብለዋል።

ሸካ ዞን ቴፒ ከተማ በርካታ ሀብቶችና ጸጋዎች ቢኖሩም ይህን ተደጋግፎ ከመጠቀም ይልቅ የመገፋፋትና ስግብግብነት በመታየቱ ከተማው ወይም ዞኑ ማመንጨት የሚችለውን ሀብት ማመንጨት አልተቻለም ነው ያሉት።

እንደ ከተማ የውሃ፣ የከተማ መብራት ችግርና የኑሮ ውድነት እንዲሁም የከተማ መኖሪያ ቤት ኪራይ ውድነት በተለይ በመንግስት ሠራተኛው ላይ ጫና እያሳደረ በመሆኑ የአመራር አካላት ቁርጠኛ ሆነው እንዲሠሩም ጠይቀዋል።

ህገ ወጥ ደላሎችና ነጋዴዎች ለኑሮ ውድነት ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ያሉት ነዋሪዎቹ ይህንንም የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው ፈር እንዲያስይዙም ጠይቀዋል።

የብልጽግና ፓርቲ እሳቤዎችና ዕቅዶች ሙሉ በሙሉ መሬት ላይ ያለመውረድ በስብሰባ መብዛት ውስን ሀብትን የሚያባክኑ ቲ-ሸርቶች ፎጣዎች ህትመቶች ትኩረት እንዲደረጉ ህብረተሰቡ ገልጿል።

የክልሉ ምክር ቤት የበጀትና የፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ የኃላሸት በላይነህ በበኩላቸው የአካባቢው ህብረተሰብ ለሠላም ለልማትና ለአንድነት ምን ዓይነት ትርጉም እንዳለው ከከተማ ከዞን ከክልል አልፎ በሀገር ደረጃ ሰላም እንዲመጣ ከቤቱ በተነሳው ሐሳብ መረዳት ችለናል ብለዋል።

በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያና ሰው ሰራሽ ኑሮ ወድነትን ለመከላከልና ለማስቆም እንዲሁም ከመሠረተ ልማት ጋር ከህብረሰቡ ለተነሳው ጥያቄና ሐሳብ እራሱ የህዝቡ የነቃ ተሳትፎና የአካባቢ ባለድርሻ አካላት ትኩረት እንደሚሻ ወይዘሮ የኃላሸት ተናግረዋል።

በመድረኩ ማጠቃለያ ሐሳብና አስተያየት የሰጡት የዞኑ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አለማየሁ ዓለሙ እንደገለጹት በውይይቱ የተነሱትን ጉዳዮችን ወስደን በህብረተሰቡ ድጋፍ እንሰራለን ብለዋል።

ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ የተነሱትን ጉዳዮችና ሌሎች ብልሹ አሰራርን በሚመለከት በአካባቢና በፋብሪካ ምርቶች ዙሪያ እንዲሁም ያልተገባ የቤት ኪራይ ጭማሪ በሚመለከት ህብረተሰቡም ከመንግሥት ጋር ተቀናጅቶ እንዲሰራ አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡ ጌትነት ገረመው – ከማሻ ጣቢያችን