ሀዋሳ፡ የካቲት 08/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የትምህርት ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አስከብር ወልዴ እንደ ክልል ለሁሉም ተማሪዎች መጽሐፍ ለማድረስ ከስድስት ሚሊየን ብር በላይ ያስፈለጋል ሲሉ ተናገሩ።
እንደ ኃላፊው ገለጻ ወጪው በመንግሥት ብቻ የሚቻል ባለመሆኑ ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ስራዎችን ለመስራት ችለናል በማለት በዛሬው ዕለት በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ አስተዳደር በወራቤ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተው የመጽሐፍ ርክክብ ባደረጉበት ወቅት ተናግረዋል። በዚህ ልክ መጽሐፍ የማሰባሰብ ስራውን በንቃት መሳተፍ ከተቻለ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል አንስተዋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ከድር ብልጽግናና ልማትን ማረጋገጥ የሚቻለው ትምህርት ሲኖር ነው፡፡ ተወዳዳሪ የሆነ ትውልድ የሚፈጠረው የትምህርት ጥራት ሲረጋገጥ ነው የሚል ሃሳብ አንስተዋል።
በ3 ዓመት ጊዜ ውስጥ የትምህርት ቤት ማሻሻያ እየተተገበረ ነው በማለት አዲሱ የትምህርት ፎኖተ ካርታ እውን የሚሆነው የመጽሐፍት ስርጭቱ በተገቢው መልኩ ሲሆን ነው። በእስካሁኑ ሒደት በመንግስትና በከተማው ህብረተሰብ አማካይነት ከ47 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ እንደተቻለ ጠቅሰዋል።
በአጠቃላይም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና መወጣት አለባቸው ሲሉም አክለዋል።
መምህራን ራሳቸውን በስልጠናና ትምህርት ማብቃት ይጠበቅባቸዋል በማለት የገጠመንን የትምህርት ጥራት ስብራት ችግር ለመቅረፍ ሁላችንም የበኩላችንን ማድረግ ይጠበቅብናል ሲሉ ገልጸዋል።
መጽሐፍቶቹ በህዝቡና በከተማ አስተዳደር በተገኘ ገንዘብ አማካይነት የተገኙ ናቸው ያሉን ደግሞ የወራቤ ከተማ ትምህርት ቤቶች ጽ/ቤት ኃላፊ በኽረዲን ሀሰን ናቸው።
5 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ከቅድመ መደበኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ያሉ መጽሐፍት ማሰራጨታቸውንም አክለዋል።
በቀጣይም የመጽሐፍ እጥረቱን ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ እንሰራለን ብለዋል።
የትምህርት ቤቱ ምክትል ርዕሰ መምህር የሆኑት ሰይፉ ሱልጣን፤ ከሆነ ተማሪዎች ከዚህ ቀደም ባጋጠማቸው የመጽሐፍ እጥረት ሳቢያ እንደሚቸገሩ በመናገር አሁን ላይ በመንግስትና በከተማው ህዝብ ትብብር አማካኝነት ችግሩን ለመቅረፍ እየተሞከረ እንደሆነና ይህም እንዳስደሰታቸው በመናገር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥም ያስችላል ብለዋል።
ያነጋገርናቸው የተማሪ ወላጆችም ልጆቻቸው በመጽሐፍ እጥረት ሲቸገሩ እንደነበር አንስተው አሁን ላይ ችግሩ ይቀረፋል ብለው እንደሚያስቡ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ ብሩክ አማረ
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ