በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ “በባህል እሴቶች፣ ሀገር በቀል ዕውቀት፣ ብዘሃ-ባህል አብሮነት፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና አሉታዊ መጤ ባህሎች” ዙሪያ ለዞን ባህል ቱሪዝምና ሰፖርት መምሪያ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት የተዘጋጀ የስልጠና መድረክ በኮንታ ዞን አመያ ከተማ ተካሂዷል።
የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ አቶ አክሊሉ ለማ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የባህል ተምሳሌት ሥራዎችን መስራት፣ ወጎችን መጠበቅና መንከባከብ፣ ክብረ በዓላትን መሰነድ፣ የኪነ- ጥበባት ሥራዎችን ማጠናከር፣ የቁሳዊ ባህሎች አጠባበቅና አጠቃቀም ሂደትን ማጠናከር እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በማስወገድ ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት ወጥ የሆነ ግንዛቤ ለመፍጠር ታልሞ የተዘጋጀ ስልጠና እንደሆነም ተናግረዋል።
በማከልም ስልጠናው የሰልጣኞችን መደበኛ ሥራዎች ለማጠናከር፣ አዳዲስ የዞን መምሪያ ሃላፊዎች እና ባለሙያዎች ግንዛቤ የሚያገኙበት እንደሆነም ገልጸዋል።
የክልሉ ታሪክ ጥናትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ለማ የብዝሃ ባህል አብሮነት፣ አካታችነት እና የህዝብ ለህዝብ ትስስር ለአገራችንም ሆነ ለክልላችን ህዝቦች ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑንና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን፣ አሉታዊ መጤ ባህሎች በዘላቂነት ለማስቀረት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት ወሳኝ ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል።
ከሰልጣኞች መካከል አቶ ቦኒ ሀዬች የክልሉ የምዕራብ ኦሞ ዞን ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ እና ወ/ሮ አለምነሽ ስለሺ የክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ የቱሪዝም ዘርፍ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የብቃት ማረጋገጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፤ ባህል የአንድ ማህበረሰብ መገለጫ መታወቂያ ስለሆነ ከሀይማኖት ተቋማት፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከወጣቱ ማህበረሰብ፣ ከፍትህ አካላትና ከተለያዩ አደረጃጀቶች ክፍል ጋር በመወያየት በቅርበትና በቅንጅት መስራት እንደሚገባና አዳዲስ ወደ ተቋሙ ለሚቀላቀሉ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች መሰል ስልጠናዎች ለዘርፉ ትኩረት ለመስጠት ትልቅ ጉልበት እንደሆነላቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
አቶ ቦኒ በማከልም እንደ አካባቢያቸው ከዚህ ቀደም ከጋብቻ ጥሎሽ ጋር ተያይዞ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በስፋት መኖራቸውን በመግለጽ በአሁን ሰዓት ህብረተሰቡ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚያገኘው ግንዛቤ መነሻ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቱ እየቀነሰ መምጣቱን ለአብነት አክለዋል።
ዘጋቢ፡ ፋሲካ ሙሉጌታ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ