የልማታዊ ሴፊትኔት መርሃ-ግብር የነዋሪዎቹን የምግብ ዋስትና ችግር ከመቅረፍ በተጨማሪ ለከተማው ልማት አይነተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የዲላ ከተማ አስተዳደር ገለጸ

የልማታዊ ሴፊትኔት መርሃ-ግብር የነዋሪዎቹን የምግብ ዋስትና ችግር ከመቅረፍ በተጨማሪ ለከተማው ልማት አይነተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የዲላ ከተማ አስተዳደር ገለጸ

ሀዋሳ፡ የካቲት 06/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የልማታዊ ሴፊትኔት መርሃ-ግብር የነዋሪዎቹን የምግብ ዋስትና ችግር ከመቅረፍ በተጨማሪ ለከተማው ልማት አይነተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የዲላ ከተማ አስተዳደር ገልጿል፡፡

የከተማው ነዋሪዎችም በበኩላቸው በመርሃ-ግብሩ ታቅፈው መስራት ከጀመሩ ወዲህ በኑሯቸው ተስፋ ሰጪ ለወጥ ማየት መቻላቸውን ተናገረዋል።

የዲላ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የዲላ ከተማ ልማታዊ ሴፊትኔትና ሥራ ፕሮጀክት ለመጀመሪያ ዙር የአካባቢ ልማት ተጠቃሚዎች የድጋፍ ገንዘብ ለማስተላለፍ ለባለድርሻ አካላት የተዘጋጀ የስልጠና መድረክ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ የከተማው ከንቲባ አቶ ዳንኤል ሽፈራው ልማት ዋጋ በጊዜ ሂደት በሚከፈል ዋጋ እንጂ ቀላልና የአንድ ጀንበር ጉዳይ ባለመሆኑ በቁርጠኝነት ያሉትን አማራጮች አማጦ በመጠቀም የኑሮ ውድነትን በማቃለል የተጀመረውን ልማት ለማስቀጠል ሁሉም ጥረት እንዲያደርግ አሳስበዋል።

2ሺህ 2 መቶ 51 የሚሆኑ ተጠቃሚዎችን በማቀፍ በወርሃ ጥር 2014 ዓ.ም ሥራው  አሀዱ ብሎ የጀመረው መርሃ-ግብሩ የተጠቃሚዎችን ኑሮ ከማሻሻል ባሻገር የከተማን ንጽህናና በአረንጓዴ ልማት ተፋሰስ ሥራን እያቀላጠፈ እንደሚገኝ የተናገሩት የከተማው አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ምንተስኖት ከበደ ናቸው።

የልማታዊ ሴፍትኔትና ሥራ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ የኋላሸት ለማ በበኩላቸው ተጠቃሚዎች በከተማው ከማሰሩት የልማት ሥራ በተጓዳኝ የኑሮ ማሻሻያና የክህሎት ስልጠናዎችን በመስጠት ተጨማሪ ሥራ ሰርተው ካገኙት ገቢ ከ3.3 ሚሊየን ብር በላይ እንዲቆጥቡ በማድረግ በመመሪያው መሰረት ከ15.5 ሚሊየን ብር ወደ ሂሳብ ደብተራቸው ገቢ መደረጉን አስገንዝበዋል።

ከተጠቃሚዎችም መካከል ወይዘሮ ውድነሽ መንገሻ፣ ታደለች ጅሎና አቶ ሣሙኤል አራርሶ ከዚህ በፊት ሰርተው ለመለወጥ ፍላጎት ቢኖራቸውም እንኳ ከአቅም ውስንነት ምክንያት ሲንከራተቱ እንደ ነበሩ አስታውሰው በመርሃ-ግብሩ ታቅፈው መሥራት ከጀመሩ ወዲህ ግን ተጠቃሚነታቸው በእጅጉ መጨመሩን ተናግረዋል።

የባንክ ሂሳብ ደብተር እንኳን እንዳልነበራቸው የሚገልጹት ነዋሪዎቹ ለቤታቸው የሚያስፈልገውን ፍጆታ ከመሸፈን አልፈው እያንዳንቸው ከ15ሺህ ብር በላይ በባንክ መቆጠብ መቻላቸው አስረድተዋል።

ዘጋቢ፡ አማኑኤል ትዕግስቱ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን