በሳምንት 7ቱንም ቀናት ግብይት የሚደምቅበት የዲላ ከተማ “ግንብ ገበያ“

በሳምንት 7ቱንም ቀናት ግብይት የሚደምቅበት የዲላ ከተማ “ግንብ ገበያ“

የጌዴኦ ዞን ማዕከል ከተማ በሆነችው ዲላ “የግንብ ገበያ” ትልቁ ገበያ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ስያሜውንም ያገኘው ቀድሞ በነበሩ ማህበረሰብ ክፍሎች ሲገበያዩ በአቅራቢያው የነበረ አንድ ግንብ ግቢ ስለነበር ያንን ምልክት በማድረግ ስያሜውን እንዳገኘና እስከዛሬ ድረስ መጠሪያ ሆኖ እንደቀጠለም የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት የንግድ ኢንስፔክሽንና ሪጉሌሽን ዳይሬክቶሬት አስተባባሪ አቶ ታደሰ ደያሶ ይናገራሉ፡፡

የአዲስ አበባ መርካቶ ማንኛውም ሰው እንደየአቅሙ ሸምቶ እንደሚወጣበትና የለም የሚባል ነገር እንደሌለ ሁሉ በዲላ ከተማ የሚገኘው “ግንብ ገበያ” ተመሳሳይ በሆነ መልኩ በዲላ ማህበረሰብ ዘንድም መገበያያ እንደሆነ በከተማው ነዋሪዎች ይነገርለታል፡፡

የግንብ ገበያው ሰፊ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት ሲሆን ከሰብል ምርቶች እስከ ፋብሪካ እቃዎች ግብይት ይካሄድበታል፡፡ ከጩኮ ከተማ እንዲሁም ከሞያሌ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ ምስራቅ ጉጂን አጠቃሎ ዋና የግብይት ማዕከል እንደሆነ አስተባባሪው ይገልፃሉ፡፡

ቦታው የግብይት ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ አካባቢዎች መጥተው የሚገበያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እንደመሆናቸው መጠን ከኢኮኖሚ ግብይት አልፎ ባህልና ቋንቋም ጭምር የሚዳብርበት ነው፡፡

ገበያው በሳምንት ሰባቱንም ቀናት ግብይት የሚደምቅበት ከፍተኛ የሆነ የንግድ እንቅስቃሴ ያለበት ማዕከል ነው፡፡

በ1998 ዓ.ም አካባቢ ገበያውን ለማዘመን ታስቦ አምስት ማህበራት በመደራጀት ቦታውን መንግስት በማመቻቸትና መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ማህበራቱ በባለቤትነት ግንባታውን በማከናወን ለተለያዩ ነጋዴዎች በማከራየት ህንፃው አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

የግንብ ገበያው በርካታ ዘርፎችን ይዟል፡፡ ሆኖም ግን ከማዕከሉ ውጪ ያሉ ግብይቶች በየዘርፉ ባለመሆኑ ምክንያት ክፍተት የታየበት እንደሆነ ጠቁመው ገበያውን በማዘመን ሸማቹ ማህበረሰብ ምቹ በሆነ መንገድ እንዲገበያይ ታስቦ እየተሰራ እንዳለ አበራርተዋል፡፡

በመጨረሻም አቶ ታደሰ ሲናገሩ ሸማቹና ሻጩ በተመቻቸ የግብይት ይዘት እንዲገበያዩ ስለሚፈለግ ከተማውን በሚመጥን መልኩ የግብይት ማዕከሉን ለማደራጀት በሚደርገው ርብርብ ላይ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ከጎናችን በመቆም የከተማችንን ውበት በጠበቀ መልኩ እንዲሰራ የሁሉም ድጋፍና እገዛ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ሐና በቀለ