ሀዋሳ: የካቲት 04/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ኢትዮጵያ ያሏትን የተፈጥሮ ጸጋዎች በአግባቡ አልምታ መጠቀም የምትችልበትን አማራጮች ከሀሣብ አመንጪነት እሥከ ተግባር በሚገለጽ አሠራር ቀልጣፋና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት የሚሠጥ ሲቪል ሠርቫንት መፍጠር እንደሚገባ ተመላክቷል።
ከዕዳ ወደ ምንዳ ሁለተኛ ዙር የሲቪል ሰርቫንት ሥልጠና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በ7ቱም ክላሥተር እየተሰጠ ሲሆን፥ በዱራሜ ማዕከል የሚገኙ ተቋማት ሲቪል ሰርቫንቶችም ሥልጠናውን መውሠድ ጀምረዋል።
በስነ-ምግባርና በቅን አገልጋይነት የተቃኘ ፐብሊክ ሰርቫንት ለለውጡ ዘላቂነት ያለው ድርሻ አይተኬ መሆኑን የገለፁት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ናቸው።
እንደ ሀገር የገጠመንን ፈተና ወደ እድል በመቀየር የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ከማሳካት አንጻር ሲቪል ሰርቫንቱ ያለው ድርሻ የጎላ ከመሆኑም በላይ፥ ጠንካራ ተቋም ስንፈጥር ጠንካራ ሀገረ-መንግስት ለመገንባት ሲቪል ሰርቫንቱ አይተኬ ሚና አለው ሲሉ ገልጸዋል።
ከ60 ዓመታት በኋላ የታሪክ እጥፋቷን የቀየረች ሀገር፥ ስንዴን ከውጭ ከማስገባት ወደ መላክ በመሸጋገር ሂደት ውስጥ ሲቪል ሰርቫንቱ የነበረውን ድርሻ ያስታውሱት ኃላፊው፥ በዲፕሎማሲው ረገድም እንደ ሀገር በተገኘው ስኬት ላይ ሲቪል ሰርቫንቱ የነበረው ድርሻ ላቅ ያለ እንደነበር ተናግረዋል።
አንገት አስደፊውን ድህነት በማሸነፍ የአድዋን ታሪክ መስራት እንደሚገባ ያነሱት ኃላፊው፥ ስልጠናው የአድዋ ታሪክ መታሰቢያ እየተዘከረ ባለበት ማግስት መሆኑ የበለጠ ለመስራት የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።
ስልጠናው በሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን፥ በሀብት መፍጠር እና ሀብት የማስተዳደር ጉዳዮችን ታሳቢ በማድረግ፥ በ 5 ቡድን ተከፍለው በሚያደርጉት ውይይት ለሁለት ቀናት እንደሚቆይ ተመልክቷል።
ዘጋቢ: ዘላለም ተስፋዬ
More Stories
በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የሚባክነውን የህዝብና የመንግሥት ሀብት ማዳን መቻሉ ተገለጸ
ቅንጅታዊ አሠራርን በማስፈን ጥምር ደን መጠበቅ፣ ማስፋትና መጠቀም እንደሚገባ ተጠቆመ
የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በማዘመን የዘርፉን ውጤታማነት ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ተገለፀ