በሐና በቀለ
አካል ጉዳተኝነት በተለያዩ ምክንያቶች ይከሰታል፡፡ ከነዚህም ጥቂቶችን ለመጥቀስ ያህል በቂ ክትባት ባለማግኘት፣ በሕክምና ስህተት፣ በአባላዘር በሽታ፣ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች፣ በእርግዝና ወቅት አለአግባብ መድሀኒት በመውሰድና ጽንስን ለማቋረጥ በሚደረግ ሂደት፣ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ይከሰታል፡፡
አብዛኛውን ጊዜ ወላጆች አካል ጉዳትን ከአምላክ ቁጣ ጋር በማያያዝ ሕፃናት የአካል ጉዳት ሲደርስባቸው ከቤት ለማስወጣትና ለማስተማር ፈቃደኛ አይሆኑም፡፡ ሆኖም ግን አሁን ላይ ከቀድሞ ይልቅ ለማህበረሰቡ በተለያዩ አቅጣጫዎች ግንዛቤ እየተሰጠ በመሆኑ መሻሻሎች ይታያሉ፡፡
በዚሁም መነሻ በሀዋሳ ከተማ የመጀመሪያ በሆነው የአይነ ስውራን ትምህርት ቤት በመገኘት ት/ቤቱ እየሰራ ያለውን ስራዎች በመቃኘት ወደ እናንተ አቅርበናል፤ መልካም ንባብ፡፡
“ሶሎን የአይነ ስውራን ትምህር ቤት” ስያሜውን ያገኘው በቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት በነበሩት በነጋሶ ጊዳዳ አያት ሲሆን በወለጋ ክፍለ ሀገር ልዩ ስሙ ጊምቢ በሚባልበት አካባቢ ሚስዩናዊያን በ1940ዎቹ ዓ.ም ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮት ባሻገር ለአይነ ስውራን የብሬል ትምህርት በሚሰጡበት ወቅት የእሳቸው ሚና ከፍተኛ ነበረ፡፡ የብሬል ትምህርት በቤተክርስቲያን እንዲሁም የአይነስውራን ትምህርት ቤት ተከፍቶ አይነስውራን እንዲማሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበራቸው፡፡ ስለዚህ መታሰቢያነቱ ለእሳቸው እንዲሆን ታስቦ በስማቸው የተሰየመ ትምህርት ቤት ነው፡፡
ድርጅቱ ሀገር በቀል ሲሆን በሲቪል ድርጅቶች ባለስልጣን ተመዝግቦ እውቅና አግኝቶ የሚሰራ ተቋም ነው፡፡
አቶ ገዛኸኝ ተስፋዬ “የሶሎን አይነ ስውራን ትምህርት ቤት” ዳይሬክተር፣ ባለቤትና መስራች ሲሆኑ ከዚህ ቀደም ለ11 ዓመታት የአይነ ስውራን ትምህርት ቤት ከፍተው ሲያስተምሩ የቆዩ ግለሰቦች ቢኖሩም የረጂ ድርጅቶች ውላቸውን በማቋረጣቸው ምክንያት መቀጠል ስላልቻሉ በአዲስ መልክ አቶ ገዛኸኝ በመረከብ ለ3 ዓመታት እንዲሁም እስከአሁኗ ጊዜ ድረስ ቀጣዩን ስራ እያስኬዱ ይገኛሉ፡፡
ትምህርት ቤቱ ስራውን ሲጀምር በ7 ተመሪዎች እንደተጀመረ አስታውሰው አሁን 20 ተማሪዎችን በመቀበል ለ2 ዓመታት ሙሉ ወጪያቸውን ኒውዘርላንድ የሚገኙ የውጭ ሀገር ለጋሽ ዜጎች በሚሰጡት የገንዘብ ድጋፍ የአስተዳደር ስራተኞችና ተማሪዎቹን የሚንከባከቡ እንዲሁም መምህራን በመቅጠር እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡
ተማሪዎችን ከሲዳማ ዙሪያና በቀድሞ ደቡብ ክልል ከመንግስት አካላት፣ እንዲሁም ከአካል ጉዳተኞች ማህበራት ጋር በመሆን እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ በመውረድ አይነስውራንን ምልመላ ካደረግን በኋላ እድሜያቸው ከ6 እስከ 12 ዓመት የሆኑ አይነስውራንን ብቻ በመቀበል በዋናነት የአማርኛ እና እንግሊዝኛ ብሬልን ማንበብና መፃፍ የማስቻል ስራ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡
ከዚያም በት/ቤቱ የሁለት ዓመት ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ ሻሸመኔ አይነስውራን ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ 7ኛ ክፍል በአዳሪነት ትምህርታቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ትምህርታቸውን ጨርሰው ሲወጡ የአካቶ ትምህርት ከተቻለ በመጡበት ወረዳና ዞን እንዲማሩ ማድረግ፤ ካልሆነ ደግሞ ሀዋሳ ላይ ባሉ የአካቶ ትምህርት ቤቶች የቤት ኪራይና አጠቃላይ ወጪያቸው ተሸፍኖ የሚማሩበት ሂደት እንዳለ ነግረውናል፡፡
ከትምህርቱም ባሻገር እነዚህ ህፃናት ከቤተሰቦቻቸው ጋር እያሉ አይነስውራን ተብለው አንድ ጥግ ተቀምጠው የሰውን እርዳታ ብቻ የሚጠብቁ ስለነበሩ እዚህ ከመጡ በኋላ በጊቢ ውስጥ እራሳቸውን ችለው እንዲቀሳቀሱ፣ ልብሳቸውን እንዲለብሱ፣ መኝታ ማንጠፍና የተለያዩ እንቅስቃሴዎቻቸውን ዕለት ዕለት እንዲተገብሩ እናደርጋለን፡፡ ይሄ ደግሞ ሌሎች ላይ ጥገኛ እንዳይሆኑና በራስ መተማመናቸው ከፍ እንዲል ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡
ተማሪዎቹ እዚህ በሚቆዩበት ወቅት ቁርስ፣ ምሳ፣ እራት እንዲሁም የማስተማሪያ ቁሳቁሶችና የደንብ ልብስ የሚሟላላቸው ሲሆን ከዚያም ባሻገር ሲታመሙ የህክምና አገልግሎትን እንዲሁም ወላጆቻቸው ሊጠይቋቸው በሚመጡበት ወቅት የግንዛቤ ማስጨበጫና የትራንስፖርት ገንዘብ ይሰጣቸዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ትምህርት ቤቱ በአጠቃላይ ከተጀመረ 14 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ከተማሩት ውስጥ በዩኒቨርስቲ ደረጃ የደረሱ እንዳሉ ገልፀው አሁን ደግሞ በ3 ዓመታት ውስጥ 200 ተማሪዎችን ለ1ኛ ደረጃ ትምህርት ማብቃት መቻላቸውን ገልፀዋል፡፡
ወላጆች አሁን ላይ ለልዩ ፍላጎት ያላቸው ግንዛቤ እየጨመረ ስለመጣ ወላጆች ደውለው ልጆቼን አስተምሩልኝ ብለው የሚጠይቁ እንዳሉ ገልፀው አሁንም ግንዛቤ ከማስጨበጥ አንጻር ይቀረናል ብዬ አስባለሁ ይላሉ፡፡
በሲዳማ ክልል የሕፃናት የብሬል ትምህርት ቤት ብቸኛ የአይነ ስውራን መሆኑን ተናግረው የሚረዳቸው አካል ቢያገኙ ወደ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከፍ ለማድረግ እቅዱ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ስለዚህ ይህንን ስኬት ወደፊት ለማስቀጠል ትምህርት ቤቱን ማስፋትና ሌሎችንም አይነ ስውራንን ለመቀበል እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን ውጭ ሀገር ካለው ረጂ በስተቀር በቋሚነት ከሀገር ውስጥ የሚረዳው ባለመኖሩ ምክንያት በዓመት ውስጥ በ20 ህፃናት ብቻ ተገድበን እየሰራን እንገኛለን ሲሉም ት/ቤቱ የተጋረጠበትን አደጋ ያስረዳሉ፡፡
“አሁን ላይ የኑሮ ውድነቱ ይታወቃል፡፡ ቀድሞ ከያዝነው በጀት ጋር አብሮ አይሄድም፡፡ አንዳንድ ግለሰቦች የምሳ፣ የእራት ፕሮግራም እንዲሁም የቤተክርስቲያን ልጆች አልባሳትን፣ የተለያዩ የምግብ ሸቀጣሸቀጦችንና የንጽህና መጠበቂያ ቁሶችን በማምጣት እያገዙን ክፍተቶቻችንን እየሸፈኑልን ነው፡፡
“ከዚያም በተጨማሪ የትምህርት ክፍሉ ጥበት፣ ወንበር፣ ጠረጴዛና ሌሎች ጉድለቶች ስላሉብን የሚመለከተው አካል ቢያግዘን ለትውልዳችንና ለሀገራችን ከዚህ በላይ እንሰራለን” ሲሉ አቶ ገዛኸኝ ገልፀዋል፡፡
መምህርት ማርያም አድነው አጠቃላይ በብሬል ዙሪያ መምህርት ነች፡፡ በካቶሊክ አይነስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት የተማረች ሲሆን ከዚያም በተጨማሪ በህግ የመጀመሪያ ዲግሪ አላት፡፡ ሆኖም ግን አይነስውራን ሕፃናት ተምረው ሀገራቸውን የሚያስጠሩ ብቁ ዜጋ ሆነው መውጣት አለባቸው በሚል ቁጭት እዚሁ ትምህርት ቤት ለ8 ዓመታት አስተምራለች፡፡
“እነዚህ ሕፃናት አሁን ላይ ለመማር ያላቸው ፍላጎት ከፍ ያለ ስለሆነ ትልቅ ቦታ ደርሰው ማየት እፈልጋለሁ” ትላለች፡፡ ስለዚህ እነዚህ ነገ ሀገር ተረካቢ ተማሪዎች የሚያስፈልጋቸውን የተለያዩ ቁሳቁሶችን በተገቢው አግኝተው እንዲማሩ መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ቢሰጣቸው የተሻለ ዜጋ ይሆናሉ ስትል መልዕክቷን አስተላልፋለች፡፡
በትምህርት ቤቱ ያገኘናቸው ተማሪዎች በእሱፈቃድ እና ዳዊት በብሬል እንግሊዝኛና አማርኛ መፃፍ እንዲሁም ማንበብ እንደቻሉ ነግረውን ለወደፊት ዳኛ እና አስተማሪ መሆን እንደሚፈልጉ ይገልፃሉ፡፡ መምህራኖቻቸውንና የትምህርት ቤቱን ኃላፊ ለተሰጣቸው እድል አመስግነዋል፡፡
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ