የበጋ መስኖ ስንዴ ፊታውራሪው

አቶ ወራቦ ዲማ የአምስት ወንድ እና የአምስት ሴት ልጆች አባት ናቸው። በዳውሮ ዞን፣ በገና ወረዳ በዲላሞ ማረቃ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ልጆቻቸውን ለማሳደግ የሚያመርቱት ምርት አልበቃ ያላቸው፤ አንገታቸውን ደፍተው ለመኖር የተገደዱ አርሶ አደር ነበሩ።

ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ለመላክ እጅ የሚያጥራቸው እና ማኅበራዊ ወጪዎች የሚያሸማቅቋቸው ደሃ አርሶ አደር በመሆናቸው ይቆጫሉ። ልጆቻቸው ጠግበው በልተው እና ትምህርት ሲማሩ ማየት ይመኛሉ። ግን በተለመደው የአኗኗር ዘዬ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ እጅግ ፈታኝ ሆኖባቸው እንደቆየ ነው የሚያወሱት።

ለወትሮው በጋ ግፋ ቢል ለጓሮ አትክልት ማልሚያ እንጂ ስንዴ የሚበቅልበት ወቅት ነው ብለው አያምኑም ነበር። በሀገር አቀፍ ደረጃ የበጋ መስኖ ስንዴ ትኩረት እንደተሰጠው ካወቁ ጀምሮ ለምን አልሞክረውም የሚል ሃሳብ አደረባቸው። ካላቸው መሬት ላይ በብርቱ ጥርጣሬ ሩብ ሄክታር ለክተው አረሱ። በእፍኛቸው ዘግነውም ዘሩበት።

ስንዴው ከክረምት ጊዜ አበቃቀሉ ፈጥኖ፤ ከበረዶ ስጋት ድኖ ምርታማ ሆኖ ደረሰላቸው። ይህን ያስተዋሉት አርሶ አደሩ በሁለተኛው ዓመት ሁለት ሄክታር የበጋ መስኖ ስንዴ ዘሩ እና ጎተራቸውን ሞሉ። ምርታማ መሆኑን እማኝ ናቸው እና በዘንድሮው ዓመት አራት ሄክታር የበጋ መስኖ ስንዴ እያመረቱ ነው።

የሰሙትን በመሞከር፤ የሞከሩትን በማስፋት የሚታወቁት አርሶ አደር ወራቦ፤ ሞክረው ያገኙትን የስንዴ ምርት ለጓደኞቻቸው በመንገር ብዙዎችን አሳምነዋል። እንዴት ተደርጎ ያሉ አርሶ አደሮችን ወትውተው በማሳመን ከመንግሥት አካላትም፤ ከግብርና ባለሙያዎች እና ከሙያ አጋሮቻቸው ምሥጋና ተችሯቸዋል።

ከዚህ በፊት በበጋ ወቅት ሥራ ፈትቼ የምኖር እና በችግር የማሳልፍ ብሆንም አሁን በራሴ ጥረት እና በባለሙያዎች ድጋፍ ከችግር ለመላቀቅ እና የቤተሰቤን ፍላጎት ለማሟላት በቅቻለሁ ይላሉ እርሳቸውም።

የወረዳውና የዞን መንግሥት እርሳቸውንና ሌሎችን ለማበረታታት የበጋ መስኖ ስንዴ ዘርፍ ላይ ድጋፍ በማድረጉም ያመሰግናሉ።

የበጋ መስኖ ስንዴ አይቸው እና ሞክሬው የገባሁበት ሥራ ነው የሚሉት አርሶ አደሩ፤ ከስንዴ በተጨማሪ እንደ ቲማቲም፣ ስኳር ድንች፣ ሽንኩርት እና ሌሎች የሥራስር ተክሎችን እንደሚያለሙ ይናገራሉ።

የበጋ መስኖ ስንዴ በተለይ ለእኛ አካባቢ ምቹ ነው የሚሉት አቶ ወራቦ፤ ስንዴው የሚደርስበት ጊዜ በቆሎ ከሚዘራበት ወቅት ቀደም ብሎ መሆኑ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ይላሉ። በዓመት ሦስትና አራት ጊዜ ለማምረት እንደታደሉም ነው የሚናገሩት።

ከዚህ በፊት ባለው ጊዜ በሄክታር 18 ኩንታል የሚያገኙ እንደነበር ጠቅሰው፤ ዘንድሮ ከሁሉም ጊዜ የተሻለ ምርት እንደሚያገኙ ተስፋ ማድረጋቸውን ይናገራሉ። የወቅቱ ጥሩነት፣ የውኃ እንደልብ መገኘት እና አስፈላጊ የምርት ግብዓቶች መጨመራቸውና አረም በጊዜው መከናወኑ ምርቱን ከፍ ያደርጋል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሄክታር ከ25 እስከ 30 እያመረቱ መሆኑን ተናግረው፤ ዘንድሮ ካመረቱት የበጋ መስኖ ስንዴ ከ100 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁ ነው የጠቆሙት።

በሚገኘው ምርት ልጆቼን አጥግቤ አበላለሁ፤ አስተምራለሁ፤ ለገበያም ምርቴን አቀርባለሁ ሲሉ ይናገራሉ። በተደጋጋሚ የበጋ ስንዴ እንዲያመርቱ ተነግሯቸው ፈቃደኛ ያልሆኑ አርሶደሮች እኔን ሲያዩ ይቀናሉ ይላሉ አርሶ አደር ወራቦ።

የበጋ ስንዴ በማልማቴ የመንግሥት ግብር ያለምንም ችግር እንድከፍል አስችሎኛል። ማኅበራዊ ጉዳይ ላይ ያለምንም ችግር ገንዘብ አወጣለሁ። ማልማት ያልቻሉት አርሶ አደሮች ግን ዓመቱን የሚዘልቁት በብድር ነው ሲሉ ይናገራሉ።

አሁን አሁን እኛን እያዩ የተቀየሩ አርሶ አደሮች አሉ የሚሉት አቶ ወራቦ፤ በአካባቢያቸው የሚገኙ ውኃማ አካላትን ተጠቅመው በትንሹም ቢሆን የጀመሩ አርሶ አደሮች እንዳሉ ይጠቅሳሉ። ወደዚህ ልማት ያልገቡ አርሶ አደሮችን እየመከርን ነው። ጠቃሚ መሆኑን እኔ ያረጋገጥኩ ስለሆነ ላገኘሁት ሁሉ እያስረዳሁ ነው ሲሉም ያስረዳሉ።

በደቦ፣ በዕድር እና በለቅሶ ሲገናኙ በተለይ የበጋ መስኖ ስንዴ እንዲያለሙ ሰዎችን እንደሚመክሩ ነው የሚናገሩት።

የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ የሚያደርጉት ለሁሉም አርሶ አደሮች ቢሆንም የበጋ መስኖ ስንዴ አምራች አርሶ አደሮች በልዩነት ድጋፍ እያገኙ ነው የሚሉት አቶ ወራቦ፤ ይህም ይበልጥ እንዲበረቱ እንዳደረጋቸው ነው የሚገልጹት።

ግብርና ባለሙያዎች ውኃ ስናጠጣ እንኳን አይለዩንም፤ የተለያዩ በሽታዎች ሲከሰቱም የኬሚካል አቅርቦት ፈጥኖ እንዲደርስ ያደርጋሉ ሲሉ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።

ባጠገባቸው የምታልፈዋ ጅረት ለግድብ የማትመች በመሆኗ ለተጨማሪ ወጪ እየተዳረጉ መሆናቸውን እንደ ችግር በማንሳት፤ ሆኖም ተስፋ ባለመቁረጥ በተሰጣቸው የውኃ መሳቢያ ከወንዟ ውኃ እየሳቡ የበጋ መስኖ ምርታቸውን ማምረት እንደማያቆሙ ይናገራሉ።

የግብዓት አቅርቦት በዘንድሮ ዓመት ሥራ ምንም ችግር እንዳልገጠማቸው የሚናገሩት አርሶአደሩ፤ የውኃ መሳቢያ ጉዳይ ብቻ እንደሚያሳስባቸው ነው የሚጠቅሱት። የመስኖ ማልሚያ የውኃ መሳቢያው ከመንግሥት ያገኙት ቢሆንም የሚሠራው በነዳጅ ስለሆነ ወጪው አይቻልም ይላሉ።

አቶ ወራቦ ዲማ ከማንም ቀድመው በቀበሌያቸው የበጋ መስኖ ስንዴን ጀምረው ያስጀመሩ የበጋ መስኖ ስንዴ ፊታውራሪ መሆናቸውን የወረዳና የዞን አመራሮች እንዲሁም የግብርና ባለሙያዎች ምስክርነት ይሰጡላቸዋል። (ኢፕድ)