ኢትዮጵያ የሌሎች ጎረቤት ሀገራትን የባሕር በር ለመጠቀም አማራጮች የማየት መብት አላት ሲሉ መምህርና የፖሊሲ ጉዳዮች አማካሪ ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ተጠቃሚነት የሌሎች ጎረቤት ሀገራት አማራጮችን ማየት አስፈላጊ ነው። ከሶማሌላንድ ጋር የተደረገው የመግባቢያ ሰነድ የቀጣናውን የኢኮኖሚያዊ ትስስር የሚያጠናክር መሆኑን አማካሪው ተናግረዋል።
ለኢትዮጵያ የባሕር በር ተጠቃሚነት ጉዳይ በአንድ ላይ ብቻ የሚተው አለመሆኑን የገለጹት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጋርም በመስማማት የወደብ ተጠቃሚነቱን ማስፋት ያስፈልጋል ብለዋል።
ለኢትዮጵያ የባሕር በር አልምቶ የመጠቀም ሂደት የበርበራና አሰብ ወደቦች ትልቅ አማራጭ መሆናቸውን ጠቁመው፤ የጂቡቲ ወደብን ጨምሮ፣ የሱዳንና፣ የላሙ ወደብ አማራጮችንም ማየት አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር በፈረመችው የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጋርም መስማማት ያስፈልጋል ያሉት አማካሪው፤ አሰብን ለመጠቀም ከኤርትራ ጋር የተጀመረውን ወዳጅነትን ማስቀጠል ተገቢ ነው ሲሉ ተናግረዋል። ሀገሪቱ ከጎረቤቶች ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እንደሚያስፈልጋት ገልጸው፤ ከሱማሊያ ጋርም በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መነጋገሩ ተገቢ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ግንኙነትን በማድረግ በመግባቢያ ስምምነቱ መሠረት በበርበራ ወደብ ላይ የምትጠቀምበትን መንገድ ማመቻቸትም እንደሚያስፈልጋት ጠቁመው፤ ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጋርም ይበልጥ መነጋገርና መስማማት የሚቻልበት ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።
የኢትዮጵያና ሱማሌላንድ ስምምነትን ተከትሎ ሱማሊያ ተቃውሞ ማንሳቷን ያስታወሱት አማካሪው፤ የመግባቢያ ስምምነቱን የሱማሊያ መንግሥት የሚቀበልበትን ዲፕሎማሲያዊ ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ሱማሊያን ለማረጋጋት ከፍተኛ ዋጋ በመክፈል በርካታ የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀቷን ገልጸው፤ አሸባሪዎች ሲቆጣጠራት ወታደሮችን በመላክ የውድ ልጆቿን ደም ዋጋ የከፈለችና አሁንም እየከፈለች መሆኑን አስረድተዋል። የባሕር ኃይል ጉዳይ ለኢትዮጵያ የባሕር ጥቅሞቿን ማስጠበቅ እንድትችልና ከሌሎች ሀገር ፈቃድ ተላቃ ራሷ እንድትጠቀም የሚያስችል በመሆኑ በራስ አቅም የምንጠቀምበት ወደብ አስፈላጊ ነው ብለዋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል።
የአፍሪካ ኅብረትም እየተሠራ የሚገኘው የኢኮኖሚ ትስስር የተለያዩ ሀገራት ነፃ የኢኮኖሚ ግንኙነትና ቁርኝት እንዲኖራቸው ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረው፤ ትስስር ኢትዮጵያ ለጂቡቲ የምትከፍለውን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በመቀነስና በባሕር በር ጉዳዮች ተሳታፊ ሆና ልትሠራበት የምትችልበት ሁኔታን ማጠናከር የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ