“ቤሾ ጉዱማሌው”
በአስፋው አማረ
የከተማውን ወጣቶች ፍላጎት መሰረት በማድረግ ነበር በሂደትም በርካታ አርቲስቶችን ለማፍራት ችሏል፡፡ ይህም ማዕከል ዛሬ “ሜሪ ጆይ” በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ ይህ ማዕከል ካፈራቸው አርቲስቶችና ድምጻዊያን መካከል በቅፅል ስማቸው ማሚላ፣ ክቺሊ እንዲሁም ምዕራፍ አሰፋ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ። በቴያትሩ ዘረፍ ደግሞ በርካታ ተዋኒያን የወጡበት ማዕከል ነው፡፡
እኛ ግን የዛሬው ትኩረታችንን ድምጻዊና የመድረክ መሪ የሆነው አፈወርቅ ገብረ መድህን ላይ በማድረግ የህይወት ተሞክሮውን ከቡዙ በጥቂቱ ልናካፍላችሁ ወደናል፡፡ ድምፃዊና የመድረክ መሪ አፍወርቅ ገብረ መድህን(ቤሾ) እንደማንኛው ኢትዮጵያዊ ጨርቅ ኳስ በመጫወት፣ ያገኘውን ተካፍሎ በመብላት እና ሌሎች በርካታ የማይረሱ ገጠመኞችንና አስደሳች የልጅነት ጊዜን ማሳለፍ ችሏል፡፡
ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል በሀዋሳ ሀይቅ ዳር ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡ 9ኛ እና 10 ኛ ደግሞ በሀዋሳ አዲስ ከተማ ትምህርት ቤት የተማረ ሲሆን በመቀጠል የመሰናዶ ትምህርቱን በሀዋሳ ታቦር ሀይስኩል አጠናቋል፡፡
ድምጻዊ አፈወርቅ ከልጅነቱ ጀመሮ ያደገው በቤተክርስቲያን ውስጥ እዝል፣ ግዕዝ እና አራራይ በመማር ሰለነበር አሁን ላለበት ሙያ ከፍተኛ እገዛ አድርጎለታል፡፡ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ትምህርት ቤት ድራማዎችን በመስራት፣ መድረክ መምራት እና በማዜም ተስጥኦውን እየለየ እና እያዳበረ የመጣበትን ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮለታል፡፡
ትምህርት ቤት ውስጥ ሚኒ ሚዲያ ላይ መስራቱ ተስጥውን ይበልጥ እንዲያጎለብት እንዳገዘውም ይናገራል፡፡ በዚህ ወቅት በሚያቀርባቸው ፕሮግራሞች፣ በዘፈን ምርጫውና በሚያንጎራጉራቸው ሙዚቃዎች ይታወቃል፡፡ በሥራውም ከተማሪዎችና ከመምህራን ይሰጠው የነበረው አስተያየት ሙያውን እንዲያሳድግ አግዞታል፡፡
ጊዜው በ1992 ዓ.ም ሜሪ ጆይ በሀዋሳ ከተማ ላይ ከመመስረቱ ጋር ተያይዞ ለድምጻዊያን፣ ለተዋኒያን፣ ለስፖርተኞች ችሎታቸውን የሚያዳብሩባቸው እና የተለያዩ ክበባት ተመስርተው ነበሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ቤሾን ጨምሮ 28 ወጣቶች አባል በመሆን ክበባቶቹ እውን እንዲሆን ምክንያት ሆነዋል። በወቅቱም “ህጻናትና ወጣቶች ማዕከል” በሚል በመጠሪያ መስራቿ ሲስተር ዘቢደር ነበረች። በሜሪ ጆይ ውስጥ አንዱ በሆነው ክበብ “ህጻናት ለህጻናት” የድራማና ድምጽዊ ክበብ ውስጥ በማስተባበሩና በመምራት አሳልፏል፡፡
በወቅቱም ሥራዎቻቸውን በእድሮች ላይ በሚያቀርቡና ስለኤች አይቪ ኤድስ ግንዛቤ በመፍጠር፣ አረጋዊያንን መርዳት፣ ቤት ለቤት በመሄድ ስለንህጽና በማስገንዘብ እና ቲያትሮችና ድራማዎችን በመስራት ግንዛቤ የመፍጠር ሥራን ይሰሩ ነበር፡፡ ይሄ ደግሞ ለቤሾ ወደ ድምጻዊነት፣ እንዲያመራና የኮሚዲያንነቱ ሙያ ውስጥ እንዲገባ መልካም እድል ፈጥሮለታል፡፡
በወቅቱ የሌሎች ድምጻዊያንን ሥራዎችን ይጫወት ነበር፡፡ እኔም በወቅቱ በብዛት በመድረክ ላይ የምትዘፍነው ዘፈን የማን ነበር? በማለት መጠየቄ አልቀረም፦ “ማንኛው ዘፋኝ ወይም ድምጻዊ ሲጀምር በሌላ ሰው ዘፈን ነው፡፡ እኔ አብዛኛውን ጊዜ የምዘፍነው ዘፈን ‘አታላይ ነች ያች ልጅ አታላይ ነች…’ የሚለውን ዘፈን ነው። እንደዚሁም የእያዩ ማንያዘዋልን ‘አይናማ የማን ነሽ አይናማ…’ የሚለውን ነበር፡፡ ሌላ ደግሞ የኬኔዲ መንገሻ አልተመቸኝ እኔን አልተመቸሽ አንቺን… የሚለውን እና ‘አካል ደማዬ አካል…’ የሚለውን እጫወት ነበር፡፡“በእነዚህ ሥራዎች ከበርካታ ሰዎች ጋር የመተዋወቅን እድልን ፈጥሮልኛል፡፡
በተለይም ደግሞ የድምጻዊ ጥላሁን ገብረየስ ‘አላሳዝንም ወይ?’ በሚለው ዘፈን ከበርካታ አድናቂዎች ጋር የተዋወኩበትን አጋጣሚ ፈጥሮልኛል። በተለይም ደግሞ ድምጻዊ ታምራት ደስታ ‘ናፍቆት ሀሳብ ሰቀቀኑ’የሚለው ሙዚቃው በመድረክ ላይ የምጫወታቸውነበር፡፡ ከዚህ ባሻገርም ድምጻዊው በጣም የምወደው ጓደኛዬ፣ መካሪዬና ባለውለታዬ ነበር” በማለት ከህዝብ ጋር የተዋወቀበትን ሁኔታ አጫውቶናል፡፡
የመጀመሪያ ነጠላ ዜማና ግጥም የሰራህበትን አጋጣሚ ብታጫውተን ?፦
“የመሰናዶ ተማሪ እያለሁ የተለያዩ ፕሮግራምችና መድረኮች ላይ የምጋበዝባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ እንደዚሁም ዩኒቨርስቲ ላይ ከተማሪዎች ጋር ለትምህርታዊ ጉዞ በምናደርግበት ወቅት ነበር ጉዱማሌ የሚለውንና የመጀመሪያውን ነጠላ ዜማዬን መስራት የቻልኩት፡፡
“አጋጣሚ የጓደኛዬ ሰርግ ላይ ለመታደም ለቦታ መረጣ በተደጋጋሚ ወደ አሞራ ገደል አመራ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ አሞራ ገደል መዝናኛ ላይ ፍቅርኛሞች ተጠራርተው ይገናኛሉ፣ ጓደኛማማቾች ይቀጣጠራሉ፡፡ እንደዚሁም የሠርግ ሰነ ስርዓት ይከውንበታል፡፡ ሁሉም ተጠራርተው የሚገናኙበት ቦታ ስለነበር ‘ነይ ጉዱማሌ’ በማለት ማዜም ችያለሁ፡፡“ከዚህ ሀሳብ በመነሳት ሀሳቡን በሚገባ አብላላሁና የግጥሙን ሀሳብ ፍሰቱን በሚገባ አስቀመጥኩት፡፡ ዜማውን ደግሞ ወደ ባሌ ዞን ሶፍኡመር ዋሻን ለመጎብኝት እየሄድን እያለ ዜማውን በስልኬ እየቀዳሁ በተደጋጋሚ እሰማው ነበር፡፡ በመጨረሻም የምፈልገውን ዜማ ማምጣት ችያለሁ፡፡
“ዜማናን ግጥሙን ካጠናቀኩ በኋላ አዲስ አበባ የተግባር ልምምድ ለማድረግ አቅንቼ ነበር፡፡ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ካሙዙ ስቱዲዮ በደንብ ተለማመድኩ፡፡ በወቅቱ ካሙዙ ጊዜ ሰላልነበረው እኔም ደግሞ ወደ ሀዋሳ መመለሻ ጊዜዬ እየተቃረበ ስለነበር የማቀናበር ሥራውን ኤፍሬም ወርቅነህ ሰርቶልኛል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ነበር የመጀመሪያዬ ሥራ ለህዝብ ማድረስ የቻልኩት፡፡ የመጀመሪያ ሥራው ለህዝብ በሚያደርስበት ወቅት ሌሎች ድምጻዊያን አዳዲስ ስራዎችን ለህዝብ ያበረከቱበት ወቅት ነበር፡፡ ለአብነት ማሚላና ኪቺሊ በጋራ ያወጡት አውባዴ የሚለው ሥራቸው በተለቀቀበት ሰሞን ቤሾም ሥራውን ለህዝብ አድርሷል፡፡ ይህ ወቅትም የቀድሞ የደቡብ ክልል ሙዚቃዎች በስፋት ለህዝብ የሚለቀቁበት እንደነበር ያስታውሳል፡፡
ድምጻዊ ቤሾ ከክሊፑ በፊት ኦዲዮው ነበር በስፋት የታወቀበት እንደነበር ይናገራል። ከዚህ በመቀጠል ነበር ክሊፑን በመስራት ለህዝብ ያደረሰው፡፡ ይህም ይበልጥ በመላ ኢትዮጵያ ህዝብ ጋር አስተዋወቀው፡፡ ድምጻዊው ከዚህ ሥራ በኋላ ሌሎች ሥራዎችን መስራት ችሏል፡፡ ለሀዋሳ ከተማ ምስረታ 50ኛ የወርቅ ኢዩቢልዩ “ፍቅር ነሽ ሀዋሳ” የሚል መጠሪያ ያለውንና ሁለተኛ ሥራውን(ነጠላ ዜማ) ለህዝብ ማድረስ የቻለው፡፡ ከዚህ ባሻገርም ከዳይመንድ ዙምባራ ጋር አባይን አስመልክቶ ሶስተኛ ሥራን በመስራት ለህዝብ ጆሮ አድርሷል፡፡ የዚህ “ኢትዮጵያ እጆችሽን ወደ እግዚአብሄር ዘርጊ ከላይ ነው ትዕዛዙ ምንም እንዳትሰጊ” የሚል መጠሪያ ያለው ነጠላ ዜማ የግጥሙና የዜማውም ባለቤት አፈወርቅ ነው፡፡
ወደ ፊት ምን አስበሀል ? ፦
“ከህዝብ በተነሳው ጥያቄ መሰረት ‘ወሌ ባራ’ በማለት ጉዱማሌ ቁጥር ሁለት ወይም በአማርኛ ሌላ ቀን በማለት ሥራው ተሰርቶ ተጠናቋል፡፡ ነይ ጉዱ ማሌ ያልኳት ልጅ ‘አይ ሌላ ቀን’ ብላኝ ሰለሄደች …፡፡ ቁጥር ሁለት ተሰርቶ ተጠናቋል፡፡ ሥራው ተጠናቆ ሲያልቅ ለህዝብ በክሊፕና በድምጽ የሚደርስ ይሆናል፡፡ “አሁን ላይ በርካታ ሥራዎችን እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ ቀደም ሲል ከአርቲስት ታምራት ጋር በመሆን የጀመርኳቸው ሥራዎች ነበሩ። በአጋጣሚ ሥራዎቻችን ጠፍተዋል የዚህ ሥራ ግጥሙ የኔ፣ ዜማው ደግሞ የእሱ ነበር፡፡ ሥራውን ለማጠናቀቅ እየሰራሁ ነው፡፡ “በተጨማሪ በቅርብ ከሚለቀቁ ሥራዎች ‘ሰመመን ትዝታ’ የሚል ስያሜ ያለው ሥራዬ ለህዝብ የሚደርስ ይሆናል፡፡ እንደዚሁም አንድ ወላይትኛ የሙዚቃ ሥራ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ ባሻገርም አንድ የሰርግ ሥራ በመስራት ላይ ነኝ፡፡ በተለይም በመዝናኛው ዘርፍ የሰርግ ፣ ልደትና የተለያዩ ዝግጅቶች ላይ በባንድ በመታጀብ ሰፊ ሥራን በመስራት ላይ እገኛለሁ” በማለት በቅርብ ጊዜ ውስጥ በአዳዲስ ሥራዎች ወደ ህዝብ በስፋት ብቅ እንደሚል አጫውቶናል፡፡
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”