የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በቀቤና ልዩ ወረዳ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮች ጋር በወልቂጤ ከተማ ውይይት በማድረግ ተወካዮችን መርጧል

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በቀቤና ልዩ ወረዳ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮች ጋር በወልቂጤ ከተማ ውይይት በማድረግ ተወካዮችን መርጧል

ከማህበረሰቡ ተወካዮች የሚቀርቡ አጀንዳዎች ለሀገራዊ መግባባት የጎላ ሚና እንደሚኖራቸው ተጠቁሟል።

በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን፣ ጠንካራ እና ቅቡልነት ያለው ሀገረመንግስት ግንባታ ለማጠናከር፣ ፍትህና እኩልነት ለማስፈን እንዲሁም ዲሞክራሲ ለመገንባት እንዲቻል ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ መቋቋሙን የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ሙሉጌታ አጎ በዚሁ ወቅት ገልፀዋል።

ኮሚሽኑ አካታች፣ ግልፅና አሳታፊ በሆነ መልኩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮችን በመምረጥ ወደ ተግባር ለመግባት ዝግጅት መጠናቀቁንም ተናግረዋል።

ለዚህም ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመፈተሽ ጠንካራና ደካማ ጎናቸውን በመለየት ወደ ተግባር መግባቱን ነው ኮሚሽነር አቶ ሙሉጌታ የተናገሩት።

ሀገራዊ መግባባትና ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር ታልሞ ለሚካሄደው ምክክር ለመሳተፍም ሆነ ለተግባራዊነቱ የቀቤና ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች እያደረጉት ላለው ተሳትፎና ላሳዩት ተነሳሽነት ኮሚሽነሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ለሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት በየደረጃው የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የበኩላቸውን እንዲወጡም አቶ ሙሉጌታ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በመድረኩ ላይ ከተሳተፉ የቀቤና ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል ኢማም ሀያቱ ሻሚል፣ ወ/ሮ ፋኢዛ አብደላ፣ አቶ ሙደሲር አብዶሼና አብድልበር ከዲር ይገኙበታል።

በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶችና አለመግባባቶች እንዲሁም የፍትሀዊነት ችግሮችን በመፍታት ዘላቂ ሰላምና ተግባቦት ለመፍጠር ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

በልዩ ወረዳው ተወካዮችን ለመምረጥ በተካሄደው መድረክ የታየው ግልፀኝነትና አሳታፊነት እንዳስደሰታቸው ገልፀው በኮሚሽኑ ለታቀዱ ተግባራት ውጤታማነት የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በመድረኩ የወጣቶች፣ የመምህራን፣ የእድሮች፣ የአርሶ አደሮች፣ የነጋዴዎች፣ የሴቶች፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የመንግስት ሰራተኞችና የሌሎችም የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን ከወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ጨምሮ ከሁሉም የልዩ ወረዳው ቀበሌያት ከተውጣጡ ከመቶ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በመወያየት ለሀገር አቀፍ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳ የሚሰጡ ተወካዮች ተመርጠዋል።

ዘጋቢ፡ ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን