የባህር በር ጥያቄ

የባህር በር ጥያቄ

በዘላለም ተስፋዬ

በአገራችን እያደገ የመጣው የህዝብ ቁጥር እና የወጪ ገቢ ንግድ ፈታኝ ሁኔታዎችን ማስተናገድ ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ ይህንን ሂደት ለመቀየር የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ሲካሔድ ቢቆይም ይህ ነው የሚባል ውጤት አላመጣም፡፡ በተለይ ለወጪ ንግዱ መፍትሔ ሊሰጡ የሚችሉ የወደብ አማራጮችን ለማግኘት ከጎረቤት ሀገራት ከፍተኛ ንግግርና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች የተካሔዱ ቢሆንም ቅሉ ግን የሚጠይቀው ወጪ የሚቀመስ የሆነ አይመስልም፡፡

በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ አቶ አለሙ ስሜ የተመራ የልዑክ ቡድን ከሐምሌ 27/2015 ጀምሮ፥ ኢትዮጵያ ተጨማሪ ወደብ የምታገኝበትን መፍትሔ ለማበጀት ወደ ሀርጌሳ ሶማሌላንድ ተጉዘው ነበር፡፡ የበርበራ ወደብን ለኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ተጨማሪ መንገድ እንዲሆን ከሶማሌላንድ ባለስልጣናት ጋር ተነጋግረዋል።

ከዚህ ጉብኝት በኋላ ይህ ልዑክ የተጓዘው ወደ ኬኒያ ነበር፡፡ ተጨማሪ የወጪ ገቢ ማሳላጫ መንገድ ፍለጋ፡፡ “በየትኛውም ዓለም ለአገሮች በፍጥነት ለማደግና ለዘላቂ ተጠቃሚነት ወሳኝ ከሚባሉት ዘርፎች መካከል መሠረተ ልማት ዋነኛ ነው፡፡ የመንገድ፣ የኤሌክትሪክና የቴሌኮም ግንኙነትን ጨምሮ፥ የአየር መስመርና ባቡርን የመሳሰሉ የሥልጡን ማኅበረሰብ መገልገያዎች መጠናከርም አለባቸው፡፡

በምንም አጋጣሚ ለወደብ መቅረብና የወደብ ባለቤት መሆን ግን ለኢኮኖሚያዊ ዕድገትም ሆነ ለአገር ዕድገት እጅግ ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው፤” ይላል “The Challenges Facing Land Locked Developing Countries” የሚል መጽሐፍ በትንተናው፡፡ ይህን አባባል ቅቡል የሚያደርገው እውነታ ዓለም ላይ ያሉ ባለከፍተኛ ኢኮኖሚ አገሮች በሙሉ የወደብ ባለቤት መሆናቸው ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚካሄድባቸው በቅልጥፍና የሚያድጉ ከተሞች የወደብ በር አላቸው፡፡ እነ አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ጃፓንና ብዙዎቹ የአውሮፓና ላቲን አሜሪካ አገሮች ለኢኮኖሚ ጥንካሬያቸው ብቻ ሳይሆን ለደኅንነታቸውም ቢሆን ወሳኝ ሀብት የባህር በር ወይም ወደባቸው ነው፡፡

ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም “አሰብ የማን ናት?” (የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ) በሚል ባዘጋጁት በጥናት ላይ የተመሠረተ መጽሐፍ ገጽ 14 ላይ እንዲህ ብለዋል፡፡ ‹‹በ2008 ዓ.ም በዓለም 44 ወደብ አልባ አገሮች ሲኖሩ ከእነዚህ ውስጥ 31 ያህሉ (70 በመቶ) ደሃ ሲሆኑ፣ አሥራ ሦስቱ ደግሞ የደሃ ደሃ የሚባሉ ናቸው፡፡ አሥራ ሦስቱም የደሃ ደሃ አገሮች በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው እንዳለ ሆኖ፣ ኢትዮጵያም ከእነዚህ አገሮች ተርታ ተመድባለች፡፡ እነዚህ ወደብ አልባ ደሃ አገሮች ወደ ውጭ የሚልኳቸው ምርቶቻቸው በአንድና በሁለት ሰብሎች ወይም በአንድና በሁለት የኢንዱስትሪ ውጤቶች ወይም ጥሬ ዕቃ የተወሰኑ ናቸው? ብለዋል፡፡ የዶ/ር ያዕቆብን ሃሳብ የሚጋሩትና የሚያጠነናክሩት ደግሞ ፖል ኮልየር ናቸው፡፡

እሳቸውም በመጽሐፋቸው “ደሃ በሆኑ አካባቢዎች የሚገኙ ወደብ አልባ አገሮች ከአራቱ የልማት ማነቆዎች በአንዱ [ወደብ አልባነት] ተጠፍረው የተያዙ ናቸው፡፡ የባህር በር ካለህ ገበያህ መላው ዓለም ነው። የባህር በር ከሌለህ ደግሞ ገበያህ የጎረቤት አገር ብቻ ነው፡፡ በጥቅሉ ወደብ አልባ አገሮች የጎረቤቶቻቸው እስረኞች ናቸው፤” ብለዋል፡፡ ጄፍሪ ሳክስ የተባሉ የምጣኔ ሀብት ምሁርም ከላይ የተጠቀሱትን ሐሳቦች በመደገፍ የባህር ጠረፍ ለኢኮኖሚ ልማትም ሆነ ፈጣን ዕድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በስፋት ዳስሰዋል፡፡ በተለይም ከቻይና ፣ ደቡብ ኮርያ፣ ጃፓን፣ ኢንዶኔዥያ፣ ሲንጋፖር፣ ወዘተ (የኤዥያ ነብሮች) አስገራሚ ዕድገት በስተጀርባ የወደብ ወይም የባህር በር፣ የምዕራቡ ዓለም ዕርዳታና ብድር ያበረከቱት አስተዋጽኦ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ ባይ ናቸው፡፡

ወደብ ይዘው ለትርምስና ለድህነት የተጋለጡ እንደ ሶማሊያና ኤርትራ ያሉ አገሮች ካልሆኑ በስተቀር፣ ብዙዎቹ ቢያንስ የተረጋጋ የኢኮኖሚ ፍሰትና የሕዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጣቸውም በተለያዩ ተንታኞች ተረጋግጧል፡፡ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ አዋዳ ካምፓስ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ኃላፊና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ወገኔ ማርቆስ እንደሚሉት፥ ጉዳዩ ለእድገታችን ወሳኝ ብቻ ሳይሆን የደህንነታችንም ህልውና በባህር በር ላይ የተመሠረተ ነው ይላሉ፡ ፡ እያደገ የመጣውን ኢኮኖሚ ማስተናገድ የሚችል አማራጭ ወደብ ማግኘት የግድ ነው የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፥ በ2014 የጸደቀውን የ30 ዓመታት የተቀናጀ የትራንስፖርት ማስተር ፕላን ወደ መሬት ለማውረድና በሃገሪቱ እያደገ ካላው ፈጣን ኢኮኖሚ አኳያ አማራጭ ወደቦችን እውን ማድረግ እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡

አቶ አለሙ ስሜ የልዑክ ቡድናቸውን ይዘው ሀርጌሳ በተገኙበት ጊዜ የጉብኝታቸውን ዓላማ ሲናገሩ፥ “ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፈጣን ኢኮኖሚ እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት ተርታ የምትሰለፍ መሆኗን ጠቁመው፥ ስለዚህም ሀገሪቱ ከጅቡቲ ዋና የባህር በር ሌላ አማራጭ ትፈልጋለች” ብለዋል፡፡ ባለፉት አስር አመታት ውስጥ የኢትዮጵያ አማካይ የወጪና ገቢ ንግድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቶ፥ አሁን ላይ 15 ሚሊዮን ቶን ደረቅ ጭነት እና አራት ቢሊዮን ቶን ፔትሮሊየም ምርት ታስገባለች፡፡ አሁን ያለውን መጠን በጅቡቲ ማንቀሳቀስ ቢቻልም ይህ ቁጥር በሚቀጥሉት አመታት እጥፍ ሊያድግ ስለሚችል አስተማማኝ የወደብ አማራጭ ማግኘት የግድ መሆኑን ዶ/ር ወገኔ ይሞግታሉ፡፡

የፖለቲካል ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት ተንታኝ የሆኑት አቶ ደያሞ ዳሌ፥ የባህር በር የማግኘት መብት ተፈጥሯዊና ዓለም አቀፍ ህጉም ይደግፈናል ባይ ናቸው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባሕር ሕግ አንቀጽ 69 ንዑስ አንቀጽ 1 እስከ 5 የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በአካባቢያቸው ካለው ባሕር የተፈጥሮ ሀብት እኩል የመጠቀም መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡ ይህም፣ ዓሳ ማጥመድን እና በባሕር ውስጥ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን ፍለጋን ጨምሮ ሌሎች ከባሕር ተፈጥሮ ሀብት ጋር የተያያዙ ሀብቶች ተጠቃሚነት መብትን ያካትታል፡፡ የዚሁ ሕግ አንቀጽ 125 ንዑስ አንቀጽ 1 እንደሚያመለክተው ደግሞ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በአካባቢያቸው ያለውን ባሕር የመጠቀም እና የመሸጋገር ዓለም አቀፍ መብት አላቸው።

ይህ መብት የባሕር በር በሌለው ሀገር፣ የባሕር በር ባለቤት በሆነው ሀገር እና በቀጣናው መካከል በሚደረግ ስምምነት ሊፈጸም እንደሚገባ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ ተመላክቷል፡፡ አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ ደግሞ እነዚህ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በስምምነት ከተደረገ የተለየ የአገልግሎት ክፍያ ከሌለ በስተቀር ለተገለገሉበት ባሕር ምንም ዓይነት የትራፊክ ታክስ ወይንም ሌላ ክፍያ እንደማይጠየቁ ይደነግጋል፡፡ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በምስረታ ቻርተሩ መግቢያ ላይ በባሕር ሕግ ጉዳዮች ላይ ባሰፈረው ሀተታ የአፍሪካ ሀገራት የባሕር በር ያላቸውን ጨምሮ ከባሕር ሊያገኙት የሚገባቸውን ጥቅም እያገኙ እንዳልሆነ ጠቅሶ፣ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ከባሕር የመጠቀም መብታቸው ሊጠበቅ እንደሚገባ እና ይህም ከዓለም አቀፍ መርህ አንጻር ሊታይ እንደሚገባ ይደነግጋል፡፡

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ ያጣችውን የባህር በር የማግኘት መብቷ ህጋዊና ተፈጥሯዊ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ እነዚህ ዓለም አቀፍ ሕጎችና የአፍሪካ ሕብረት ድንጋጌዎች ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ለመሆናቸው አሻሚ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የአፍሪካ ቀንድ ሲሆን፣ ይህም የጅቡቲ፣ የኤርትራ እና የሶማሊያ የባህር ዳርቻን ያጠቃልላል። በሱዳን እና በኬንያ በኩል ያለው መስመርም ሌላው የባሕር በርን ለመጠቀም የሚያስችላት አማራጭ መንገድ ነው። በሌላ አነጋገር የመንግስታቱ ድርጅት በ1982 ባወጣው የባሕር ህግ አንቀጽ 69 የተጠቀሰው ድንጋጌ፣ ከአንቀጽ 125 እስከ 132 የተገለጹት ድንጋጌዎች እና አንቀጽ 148 የኢትዮጵያን የባሕር መውጫ መብት የሚመለከቱ ናቸው።

በተለይ ይላሉ አቶ ደያሞ፥ በኢትዮጵያ እና የኤርትራ ቅኝ ገዢ በነበረችው ጣሊያን መካከል የተደረጉት ስምምነቶች እና የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት በ1964 የቅኝ ግዛት ውሎችን ማጽናቱ ለኢትዮጵያ የባሕር መውጫ መጥፋት በምክንያትነት ይጠቅሳሉ፡፡ እነዚህ ስምምነቶች ቢኖሩም በሌላኛው ወገን በመጣሳቸው ሕጋዊ ተፈጻሚነት እንደሌላቸው በማስረጃ አስደግፈው አስቀምጠዋል፡፡ ስምምነቶቹ ሕጋዊነት የሚያጡባቸውን መሰረቶችም ሲጠቅሱም ጣሊያን እ.አ.አ በ1935 ኢትዮጵያን ዳግም ስትወርር የመጀመሪያውን ስምምነት መጣሷን ይገልጻሉ፡፡

በዚህ ረገድ የቪየና የስምምነት ሕግ አንቀጽ 60 (1) የሁለትዮሽ ውልን በአንደኛው አካል መጣስ ሌላው አካል ለውሉ እንዳይገዛ እና ውሉን የጣሰውን አካል የመክሰስ መብት ይሰጠዋል፡፡ በዚህም መሰረት የ1900፣ 1902 እና የ1908 ስምምነቶች በሌላኛው አካል ስለተጣሰ ተፈጻሚነት እንደሌለው ኢትዮጵያ ተከራክራለች፤ ይህ ደግሞ የአልጀርሱንም ስምምነት ዋጋ ያሳጣዋል፡፡

ሁለተኛ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ1950ዎቹ ምክረ ሃሳብ እና የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ዳግም በኮንፌዴሬሽን መዋሀድ ‘የኢትዮጵያን የባሕር የማግኘት መብት’ ለመጠየቅ መሰረት ሊሆን የሚችል ስምምነት ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል አመላክተዋል፤ እንደዚህ ዓይነቶቹ ተጨባጭ እውነታዎች እና የዓለም አቀፍ የሕግ ድንጋጌዎች የአልጀርሱ ስምምነት ህጋዊ መሰረት እንደገና እንዲገመገም ጥያቄ እንደሚያስነሳ ጠቁመዋል።