ሕብረብሔራዊ አንድነታችን ሊጎለብት የሚችለው ብዝኃነትን እንደ ሥጋት ሳይሆን እንደ ጸጋ በመቀበል ማስተናገድ ሲቻል ነው
ሕብረብሔራዊ አንድነታችን ሊጎለብት የሚችለው ብዝኃነትን እንደ ሥጋት ሳይሆን እንደ ጸጋ መቀበል ሲቻል እንደሆነ የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ዛህራ ሁመድ ገለጹ፡፡
18ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን አስመልክቶ በተዘጋጀ የአሠልጣኞች ስልጠና ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የተከበሩ ወ/ሮ ዛህራ ሀገራችን ኢትዮጵያ የረዥም ዘመናት የብዝኃነት፣ የአብሮነትና የመቻቻል ባህልና ታሪክ ያላት አገር ስትሆን ሕዝቦቿን በበሳል የአመራር ጥበብ፣ በቀና አስተሳሰብና ለዘመናት አስተሳስረውን በኖሩት የጋራ እሴቶቻችን ምክንያት ችግሮቹን በመሻገር የአገራችንን አንድነት ማስቀጠል እንደተቻለ አስገንዝበዋል፡፡
የተከበሩ ወ/ሮ ዛህራ አያይዘውም ለፌዴራል ሥርዓቱ ዋስትና የሆኑ ጠንካራ ተቋማት በሚፈለገው ደረጃ አለማደጋቸው፤ ፌዴራላዊ አስተሳሰብና እሴቶች እያደጉ እንዲሄዱ የሚያስችሉ ተግባራት በተገቢው አለመከወናቸው፤ በየደረጃው የሚያገጥሙ ችግሮችን የፌዴራል ሥርዓቱን በሚያጠናክር አግባብ በንግግር እና በውይይት እየፈቱ የሚኬድበት ሥርዓት ደካማ መሆኑ፣ ብዝኀነትን እንደሥጋት የመቁጠር አዝማሚያዎች መኖራቸው፣ የፌዴራል ሥርዓት ግንባታ ሂደታዊ መሆኑን በተገቢው አለመገንዘብና ሁሉም ጥያቄዎች በአንድ ጊዜ እንዲፈቱ የመፈለግ አመለካከቶች የሥርዓቱ ፈተናዎች ሆነው መቀጠላቸውን ጠቅሰው የሥልጠናው ዋና ዓላማም እነዚህን እና ሌሎች እንደየአካባቢው ሁኔታ የተፈጠሩ ተግዳሮቶችን ነቅሶ በማውጣት በመፍትሔዎቻቸው ላይ ወደ ተግባር የሚያስገባ ግንዛቤ ለመያዝ፣ እንዲሁም ሕብረብሔራዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት የሰላም መገንቢያ መሣሪያ መሆኑን የጋራ መግባባት ለመፍጠር እንደሆነ አስረድተዋል።
የተከበሩ አፈ ጉባኤ በመጨረሻም ሠልጣኞች ሥልጠናውን በከፍተኛ ንቃትና ተሳትፎ እንዲከታተሉ አሳስበው መድረኩ በይፋ መከፈቱን አብስረዋል።
የዘንድሮው የኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል “ብዝኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል በሱማሌ ክልላዊ መንግሥት አስተናጋጅነትና በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት ይከበራል፡፡
ምንጭ፡ በፌዴሬሽን ምክር ቤት
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ