ሀዋሳ ከተማ ጌታነህ ከበደን አስፈረመ

ሀዋሳ ከተማ ጌታነህ ከበደን አስፈረመ

የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫን በማንሳት ከክልል ክለቦች ፈር ቀዳጅ የሆነው ሀዋሳ ከተማ በሀገራችን እግር ኳስ ባለፉት 17 ዓመታት ከታዩት ምርጥ የፊት መስመር ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነውን ጌታነህ ከበደን አስፈርሟል።

አንጋፋው አጥቂ ከፋሲል ከነማ ጋር የነበረው ውል መጠናቀቁን ተከትሎ ቀጣዩ ማረፊያ የሀዋሳ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ሆኗል።

ጌታነህ ከበደ በፋሲል ከነማ ከነበረው የሁለት ዓመት ቆይታው በተጨማሪ ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ ለደቡብ ፖሊስ፣ ደደቢት፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ለወልቂጤ ከተማ እንዲሁም ከሀገረ ውጪ ደግሞ ለደቡብ አፍሪካው ክለብ ቢድ ዌስት ተጫውቶ ማሳለፉ ይታወሳል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ራሱን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያገለለው አጥቂ፤ በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ 3 ጊዜ ኮኮብ ግብ አግቢ ሆኖ ያጠናቀቀ ሲሆን 2 ጊዜ ደግሞ የኮኮብ ተጫዋች ሽልማትን ማግኘት ችሏል።

በዚህ ክረምት አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን የሾሙት ሀይቆቹ፤ ለበርካታ ዓመታት ከጌታነህ ከበደ ጋር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አብሮት የተጫወተውን አማካዩን ሽመልስ በድጋሚ ማስፈረማቸው ይታወሳል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ