የፍትህ ተቋማት ተገልጋዩን ህብረተሰብ በሚመጥን መልኩ ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ ገለፁ
የፍትህ ትራንስፎርሜሽንና የፍርድ ቤቶች ጥምረት የ2017 በጀት አመት አፈፃፀምና የ2018 በጀት አመት የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ የምክክር መድረክ በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የፍትህ ተቋማት ብዙ ተገልጋይና ፍላጎቶች ያሉት ስለሆነ ይህንኑ በሚመጥን መልኩ አገልግሎት ለመስጠት በቅንጅት መስራት ይገባል።
አፈ ጉባኤዋ፤ ተቋማት ቀልጣፋ፣ ፈጣን እና ዘመናዊ የፍትህ ስርዓትን በመዘርጋት አለም የደረሰበትን የቴክኖሎጂ አቅምን በመገንዘብ ጥምረቱ ባሉበት በመሆን በየወቅቱ የተሰሩትን ተግባራት መገምገም ይገባል ሲሉ ገልፀዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት የተሰጣቸው የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ጊዜ ባለመስጠት በአግባቡ መቅረፍ ያስፈልጋል ሲሉ ዋና አፈ ጉባኤዋ አሳስበዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትና የጥምረቱ ሰብሳቢ አቶ ኤርሲኖ አቡሬ በበኩላቸው፤ ጥምረቱ በበጀት አመቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በጋራ በመሆን ከዚህ በፊት በፍትህ ዘርፍ ላይ ይስተዋሉ በነበሩ ችግሮች ላይ የመፍትሔ እርምጃ መወሰዱን ገልፀዋል።
ተከሳሽና ምስክር በወቅቱ ማቅረብ፣ የተጠርጣሪ አያያዝ፣ የተጠርጣሪ ዋስትና ማክበርና በማረሚያ ተቋማት የሚታዩ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ችግሮች መቀረፋቸውን አቶ ኤርሲኖ ተናግረዋል።
በቀጣይ በጀት አመት በዳኝነትና በፍትህ አሰጣጥ አገልግሎት ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን በመቅረፍና ተጠያቂነትን በማረጋገጥ የፍትህ ተቋማት በተቀመጠላቸው ስልጣንና ተግባር መሰረት እንዲሰሩ ይደረጋል ብለዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትም የፍትህ ትራንስፎርሜሽንና የፍርድ ቤቶች ጥምረትን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ዜጎች ወጪ ቆጣቢና ከእንግልት ነፃ በሆነ መልኩ ፍትህን ማግኘት እንዳለባቸው ገልፀው፤ ለዚህም የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ነው ያመላከቱት።
ዘጋቢ፡ ፍስሃ ክፍሌ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በተገልጋይ እርካታና በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ የፍትህ ትራንስፎርሜሽንና የፍርድ ቤቶች ጥምረት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተገለጸ
የዜጎችን ህይወት በማቀራረብ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ከሚረዱ ጉዳዮች አንዱ የበጎ ፈቃድ ሥራ መሆኑ ተጠቆመ
ሙስሊሙን ማህበረሰብ ተጠቃሚ በሚያደርጉ ተግባራት ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ አዲስ የተመረጡት የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት አባላት ገለፁ