የዜጎችን ህይወት በማቀራረብ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ከሚረዱ ጉዳዮች አንዱ የበጎ ፈቃድ ሥራ መሆኑ ተጠቆመ

የዜጎችን ህይወት በማቀራረብ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ከሚረዱ ጉዳዮች አንዱ የበጎ ፈቃድ ሥራ መሆኑ ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን ህይወት በማቀራረብ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ከሚረዱ ጉዳዮች አንዱ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ገለጹ፡፡

የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ የተመራ ልዑክ ቡድን በጋሞ ዞን ገረሴ ከተማ አስተዳደር የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አካል የሆነውን የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታ ድጋፍ አስጀምረዋል።

የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ በዚህ ወቅት እንዳሉት የዜጎችን ህይወት በማቀራረብ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ከሚረዱ ጉዳዮች አንዱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መመራቱን ገልፀዋል።

ምክር ቤቱ በተለያዩ መዋቅሮች እንደ ክልል የተጀመረውን ክረምት በጎ ተግባር ባህል ለማድረግ በገረሴ ከተማ አስተዳደር የአንዲት አቅመ ደካማ እናት ቤት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰርተው ለማስረከብ ማስጀመሩን ተናግረዋል።

ለእንደነዚህ ያሉ እናቶች መድረስ ከፈጣሪ በረከት ማግኛ፣ ፓርቲው የያዘውን ዓላማ ማሳኪያና የዜጎች ህይወት መቀየሪያ ተግባር ስለሆነ ሁሉም በእውቀት በጉልበት ያለውንና ሀሳቡን በመለገስ እንዲተባበር ጥሪ አስተላልፈዋል።

የገረሴ ከተማ አስተዳደር ዋና ከንቲባ አቶ ኤርማያስ እሸቱ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት በማስተላለፍ የክልል ምክር ቤቱ ለዜጎች ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ በመሆኑ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ በዚህ ክረምት ከሃያ በላይ ቤቶችን ለአቅመ ደካሞችና ጧሪ ላጡ ሰርቶ በማስረከብ የብልጽግና ጉዞ እውን ያደርጋል ብለዋል።

የቤት ግንባታ ድጋፍ የተጀመረላቸው ወ/ሮ አልብቶ ቦላ በተደረገላቸው ድጋፍ የተሰማቸው ደስታ ገልፀው ድጋፍ ያበረከቱ አካላትን አመስግነዋል።

6 ልጆችን በሞት አጥተው ጧሪ በሌላቸው ወቅት ለደረሱላቸው ወገኖች ፈጣሪ ዕድሜ እንዲያራዝምላቸው መርቀዋል።

ዘጋቢ፡ ተነሳ ተረፈ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን