“ነጠላ በ5ዐ ሣንቲም ሸጫለሁ”

በአብርሃም ማጋ

የ85 ዓመት አዛውንቱ “ሥራ ከሌለ ህይወት ምን ህይወት? በሚለው ጥያቄ አዘል አስተያየት ሃሳባቸውን ይጀምራሉ፡፡ ሥራ ከሌለ የሰው ልጅ የሚገባበት ይጠፋዋል በማለትም ያክላሉ፡፡ ምን ተበልቶ፣ ተጠጥቶ፣ ተለብሶ እና የት ታድሮ በማለትም ይቀጥላሉ። ሥራ በመጥላት፣ በሥርቆት ፣ በልመና፣ በጥገኝነት፣ በእርዳታ የሚኖር ሰው በህይወት እንዳለ አይቆጠርምም ይላሉ፡፡ እድሜና የጤና ሁኔታ እስካልገደበ ድረስ በራስ ላብና ወዝ ከማደር ይልቅ በድህነት፣ በበታችነት፣ በረሃብና በእርዛት ለመኖር ከወሰነ ሰነፍ ሰው ይልቅ የሞተ ሰው እንደሚሻልም ያብራራሉ፡፡

መነሻችንን መሠረት በማድረግ የአዛውንቱን ምርጥ ተሞክሯቸውን ልናስቃኛችሁ ወደናል፤ መልካም ንባብ፡፡

አቶ አበራ አለሙ የተወለዱት በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት በጋሞ ጐፋ ጠቅላይ ግዛት፣ በጨንቻ ዙሪያ ወረዳ፣ በሚገኝ ቀበሌ ነው፡፡

በወቅቱ ለትምህርት የሚሰጠው ግምት በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ የተማረ የት ደረሰ በሚል ሀሳብ ለመማር አለመታደላቸውን ይገልፃሉ፡፡

ሆኖም እሳቸው በአሥራዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ እያሉ አባታቸው የሥራ እገዛ እንዲያደርጉላቸው በድሮው አጠራር ባሌ ጠቅላይ ግዛት፣ ጐባ ከተማ ይዟቸው ይሄዳሉ። ሥራውም የሽመና ሥራ ነበር። መቼም የሽመና ሥራ በማህበረሰቡ ዘንድ ከጥንት ጀምሮ ተያይዞ የመጣ ባህላዊ እውቀት እንደሆነ ይታመናል፡፡ በመሆኑም ከልጅነታቸው ጀምሮ ከአባታቸው ጐን ሆነው ሥራውን ጀመሩት። በዚሁ 7 ዓመታት ከሠሩ በኋላ ወደ ትውልድ ቦታቸው ተመልሰው ትዳር ይመሰርታሉ፡፡

ትዳር መስርተው በሀገር ቤት አንድ አመት ከቆዩ በኋላ በሽመና ሥራ ለመሠማራት አስበው ወደ ሸበዲኖ ወረዳ ወደ ለኩ ከተማ አቀኑ፡፡ እዚያም ሥራውን ጀመሩ፡፡ ይሁን እንጂ ሥራው አዋጭነቱ አጥጋቢ ሳይሆን ቀረ። ምክንያቱም ገዢ ጠፍቶ ሳይሆን በወቅቱ በነበረው የዋጋው ርካሽነት የተነሳ ነው፡፡ አንድ ነጠላ 5ዐ ሳንቲም፣ ጋቢ ደግሞ ሁለትና ሶስት ብር ነበር የሚሸጠው፡፡

በከተማዋ ለ3 ዓመታት እየሠሩ ከቆዩ በኋላ ጥለው ወደ ትውልድ ሀገራቸው ተመለሱ፡፡ የግብርናውን ሥራ በርትተው እየሠሩ የንግድ ሥራቸውን አብረው ማጧጧፍ ጀመሩ፡፡ የንግድ ሥራቸው እራሳቸው በሽመና ከሚሠሯቸው ባህላዊ ልብሶች በተጨማሪ ሌላም ልብሶች ገዝተው ለገበያ ማቅረብ ነበር፡፡ በወቅቱ ሌላ የማጓጓዣ ዘዴ ባለመኖሩ በርካታ ልብሶችን በእራሳቸው ተሸክመው ወደገበያ ያደርሳሉ፡፡ አንዳንዴ ገበያ ፍለጋ 6 ሰዓት ሙሉ የሚያስኬድ መንገድ ይጓዛሉ፡፡ ሥራው አድካሚ ይሁን እንጂ አዋጪ እንደነበር አቶ አበራ ሳይናገሩ አላለፉም፡፡

ነገር ግን በጥሩ ሁኔታ እየኖሩ ከታላቅ ወንድማቸው ጋር አለመግባባት ተፈጠረ። የአለመግባባቱ ምክንያትም ወንድማቸው ሁሉም ነገር ለእኔ በማለት የሚፈጥረው ስግብግብነትና የራስ ወደድነት ነበር፡፡ በዚሁም ተበሳጭተው ሥራቸውን ትተው ወደ ሃዋሣ መጡ፡፡ ሃዋሣ እንደመጡም የሽመና ሥራቸውን በአዲስ መልክ ጀመሩ፡፡ ይሁን እንጂ በየጊዜው እየተመላለሱ ልጆቻቸውን፣ ባለቤታቸውንና ዘመዶቻቸውን ከመጠየቅ አልቦዘኑም ነበር፡፡ በሽመና ሥራ የተካኑ ባለሙያ በመሆናቸው የሲዳማ ጐንፋ፣ ቡሉኮ፣ ቆሎ፣ ነጠላ፣ ጋቢ እና የሃገር ቤት ባህላዊ ልብሶችን በትእዛዝ ሠርተው ይሸጣሉ፡፡

ለሰው ልጅ /ለደንበኞቻቸው/ ትልቅ ክብር የሚሰጡ፣ ታጋሽና ትሁት በመሆናቸውም ታዋቂነታቸውና ተፈላጊነታቸው እየጨመረ መጣ፡፡ በተጨማሪም የሥራዎቻቸው ጥራትና ዋጋ ተመጣጣኝ በመሆኑ ብዙ ደንበኛ ለማፍራት በቁ፡፡ ስለእሳቸው አንዱ ለአንዱ በሚሰጠው መነሻ ከሐዋሣ ከተማ አልፎ በአካባቢዋ ሥማቸው እየገነነ መጣ፡፡

አሁንም ቢሆን በ85 ዓመታቸው በበርካታ ደንበኞች ታጥረው እቤታቸው እያመረቱ ይሸጣሉ፡፡ አቶ አበራ በ1973 ዓመተ ምህረት ያላሰቡት መጥፎ ክስተት እንዳጋጠማቸው ይገልፃሉ፤ ይህም ለ7 ዓመታት በማረሚያ ቤት እንደቆዩ ያደረገ ነበር፡፡

በወቅቱ በሸማኔዎች ማህበር ተደራጅተው ከሚሠሩት በተጨማሪ ማታ እቤታቸው በሚሠሩት የሽመና ሥራ ከሌሎቹ ሻል ያለ ገቢ ያገኙ ነበር፡፡ አንድ ቀን ጐረቤታቸው 5ዐ ብር እንዲያበድሩት ጠይቋቸው ያበድሩታል። በሌላ ጊዜ ያንን ሳይመልስ ሌላ ተጨማሪ የ50 ብር ብድር ይጠይቃቸዋል፡፡ ሁለተኛውን ብድር ሲጠይቅ እቃ ይዞ ስለነበር የውስጡን ሳይናገር ይህንን እቃ ወስደው ይስጡኝ አላቸው፡፡ እቃው ምን እንደሆነ ሳይጠይቁት 5ዐ ብር አውጥተው ይሰጡታል፡፡ እቃውን በእጃቸው ላይ ጥሎ ሲሄድ ሽጉጥ ነበር። ያላሰቡት ነገር ቢሆንም በ100 ብራቸው ሽጉጡን የራሳቸው አድርገው እቤት ይደብቃሉ፡፡

ከዚያም ግለሰቡ ሄዶ በወቅቱ ለነበሩት የአብዮት ጥበቃዎች እቤታቸው ሽጉጥ አለ ብሎ ይጠቁማል፡፡ ጥበቃዎቹ አንድ ቀን ማታ በሮንድ ጥበቃ ላይ እያሉ ደርሰው ሽጉጡን አምጣ ብለው አንበረከኳቸው፡፡ ተንበርክከው ቆይተው ጉልበታቸው ከተላላጠ በኋላ እቤት ሄደው ሽጉጡን አውጥተው አስረከቧቸው፤ አስረክበውም ከሌላ መዘዝ አልዳኑም፡፡

ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው ታሰሩ። ነገሩ እየከረረ መጥቶ የ7 ዓመት ፍርድ ተፈርዶባቸው ወደ ሐዋሣ ማረሚያ ቤት ገብተው ከ1973 ዓ.ም እስከ 1979 ዓ.ም በማረሚያ ለመቆየት ተገደዱ፡፡

በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ግን ያልጠበቁት ጥሩ ነገር አጋጠማቸው፡፡ የሽመና ሥራ ለእራሳቸው እየሠሩ ሌሎች ታራሚዎች እንዲያሰለጥኑ ተፈቀደላቸው፡፡

በመሆኑም በፆታ፣ በዘርና በሐይማኖት ሳይገደቡ ማረሚያ ቤት ያሉትን ሁሉ የሽመና ሥራ ማስተማርና ማሰልጠን ጀመሩ፡፡ በዚሁም በሐዋሣ ማረሚያ ተቋም ለመጀመሪያ ጊዜ የሽመና ሥራ አስጀማሪ ለመሆን በቁ። በርካታ ታራሚዎችም ሙያውን ለምደው እየሠሩ በመሸጥ ጥሩ ገቢ ማግኘት ጀመሩ። በሚያገኙት ገቢም ቤተሰቦቻቸውን እየረዱና ተቀማጭ እያስቀመጡ ሃብት እስከማፍራት ደርሰዋል ይላሉ፡፡

እሳቸውም በግላቸው በሚሠሩት ሽመና ሥራ ቀደም ሲል እቤታቸው ሆነው ከሚያገኙት የተሻለ ገቢ በማግኘት ቤተሰቦቻቸውን በአግባቡ ማስተዳደር ችለዋል፡፡

1979 ዓ.ም ከማረሚያ ቤት ከተፈቱ /ከተለቀቁ/ በኋላም ጐድጓዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እቤታቸው ሆነው መሥራት ጀመሩ፡፡ የከተማዋ አብዛኛው ህዝብ ደንበኞቻቸው እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ ለዚህም ይመስላል “ለህዝቡ ነው እኔ የማገለግለው” ሲሉ የተደመጡት፡፡

በህይወታቸው ከሰው ጋር ተጣልተው እንደማያውቁም ይናገራሉ፡፡ ለሥራቸው ያላቸውን ፍቅር ሲገልፁም፡- “ሥራዬን አከብራለሁ፣ እንደህይወቴ አያለሁ” በማለት ነው፡፡ ይህንን ሲያብራሩም ሥራዬን የምወደው ኑሮዬ በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡ ልጆቻቸውን ያሳደጉት ሥራ በመሥራታቸው እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡

አቶ አበራን በህይወታቸው ላይ የመጣው ለውጥ ምን እንደሆነም ጠይቀናቸው ነበር። የሰጡን ምላሽ ቢኖር “ልጆቼን በሥርዓት አስተምሬና አሳድጌ እራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ለእኔ ከፍተኛ ለውጥ ነው” ይላሉ፡፡

በዚሁም የ6 ወንድ እና 3 ሴት በድምሩ የ9 ልጆች አባት ሲሆኑ ሁሉንም አስተምረዋል። ልጆችን የማስተማር ከፍተኛ ፍላጐት እንዳላቸው የሚናገሩት ባለታሪካችን “እኔ ሳልማር ቀርቼ የተበደልኩት ሳያንስ ልጆቼ መበደል የለባቸውም” በሚል በቁጭት ልጆቻቸውን ማስተማራቸውን ገልፀውልኛል።

የልጆቻቸው የትምህርት ሁኔታ ሲታይ የመጀመሪያ ወንድ ልጃቸው በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቆ ጨንቻ ወረዳ የትምህርት ቤቶች ጽ/ቤት ሐላፊ፣ ሁለተኛው ወንድ ልጃቸው በማስተርስ ዲግሪ ተመርቆ ሲዳማ ክልል ውሃ ልማት ቢሮ ይሠራል፡፡ 3ኛው ወንድ ልጃቸው የቴክኖሎጂ መሐንዲስ ነው፡፡ 4ኛ ወንድ ልጃቸው በአካውንቲንግ ትምህርት በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቆ የጨንቻ ወረዳ ንግድ ባንክ ስራ አስፈፃሚ ነው፡፡ 5ኛው ወንድ ልጅ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን የመጨረሻው ወንድ ልጃቸው በዲግሪ ተመርቆ መብራት ሃይል ውስጥ ይሠራል፡፡ ከሴቶቹ የመጀመሪያ ልጅ ውጭ ሃገር ዱባይ ትኖራለች፡፡ 2ኛዋም በዲግሪ ተመርቃ የመንግስት ስራ ላይ ተመድባ እየሠራች የምትገኝ ሲሆን የመጨረሻዋ ግን ገና ተማሪ ናት፡፡

አቶ አበራ አሁን ሥራቸውን አጋዥ በሌለበት ለብቻቸው በባህላዊ መንገድ ይሠራሉ፡፡ በ85 ዓመታቸው ዛሬም ጠንክረው በመሥራት ያከናውናሉ፡፡ ጠዋት ቁጭ ካሉ ቀኑን ሙሉ እረፍታቸው የምሳ ሰዓት ብቻ ነች፡፡

የአዛውንቱ ተሞክሮ በሌሎቹ ዘንድ መለመድ እንዳለበት እየጠቆምን የዛሬን በዚሁ ቋጨን ሠላም፡፡