በኢያሱ ታዴዎስ
በሐዋሳ ከተማ በስፋት ትታወቃለች። ልበ ቆራጥ፣ ትጉህ፣ በተስፋ የተሞላች ሴት ናት። በፈገግታ የታጀበው ውብ የፊቷ ገጽታ፣ በተስፋ ስለመሞላቷ ያሳብቃል። አንደበተ ርዕቱም ነች። ስታወራ በምርጥ ደራሲ የተጻፈን ልቅም ያለ ልብወለድ የምታነብ ነው የምትመስለው። ቃላት አጣጣሏም ቃለ ተውኔት የምታነበንብ ድንቅ ተዋናይት ያስመስላታል፡፡ ንግግሯም ለሰሚ ብርታትና ወኔን ያጋባል።
በንግግሯ መሃል የአምላኳን ስም አንስታ አትጠግብም። እዚህ ያደረሰኝ ማን ሆነና በሚል ስሜት። በሴትነቷም ኩራት ይሰማታል። “የእኔ ፍላጎት ሴት ልጅ ያለማንም እገዛ በራሷ ጥረት ስኬታማ መሆን እንደምትችል ማሳየት ነው” ትላለች ከሕይወት ልምዷ በመነሳት።
በእርግጥም ዛሬ ለሌሎች አርዓያ መሆን የምትችል ሴት ናት። ሰላማዊት እዚህ ደረጃ ከመድረሷ በፊት ብዙ አስቸጋሪ ጊዜያትን አልፋለች። አንዳንዶቹ ለሴት ልጅ ከባድ የሆኑ የፈተና ጊዜያት ነበሩ።
ለዚህ ነው መሰለኝ የኃላ ታሪኳን በምልሰት እያስቃኘችኝ ድንገት እንባ የቀደማት። እነዚያ ጊዜያት ግን ዛሬ ለመድረሷ መንደርደሪያ ናቸውና አብዝታ ትወዳቸዋለች። የትናንት የትዕግስትና የትጋት ፍሬዋን እየበላችም ትገኛለች።
ወጣት ሰላማዊት ታደሰ ውልደትና ዕድገቷ በሐዋሳ ከተማ ነው። አባቷ የመንግስት ሰራተኛ፣ እናቷ ደግሞ የቤት እመቤት ናቸው። በቤተሰባቸው ካሉ አምስት ልጆች ሰላማዊት ሁለተኛ ብትሆንም በእንክብካቤ ነው ያደገችው። ወላጆቿን ጨምሮ ታላቅ ወንድሟም ሆነ ሌሎቹ ሶስት ታናናሽ እህቶቿ ፍቅር እየለገሷት በልዩ እንክብካቤ አድጋለች።
ለዚህም ይመስላል በቤት ውስጥ ምንም ስራ መስራት አትፈልግም ነበር። ወላጆቿ ስራ ሲያዟትም መከወን ያቅታት ነበር። በዚህም ምክንያት ወደፊት የሚገጥሟትን ፈተናዎች ተጋፍጣ ትልቅ ደረጃ ትደርሳለች ብሎ የጠበቃትም አልነበረም። ግን ደግሞ ቤተክርስቲያን የምታዘወትር ጭምት ሴት ነበረችና በብዙ ሰዎች ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፋለች።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በሐዋሳ ቤተክህነት ትምህርት ቤት ተምራለች። 9ኛ እና 10ኛ ክፍል ትምህርቷን ደግሞ በሐዋሳ ታቦር አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትላ ጨርሳለች። ከዚህ በኋላ በቀጥታ የገባችው ወደ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ነበር።
በቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ በጸሃፊነት የትምህርት ዘርፍ ተምራ ተመረቀች። ከዚህ በላይ ግን በትምህርቷ አልዘለቀችም። ኮሌጅ ሶስተኛ ዓመት ተማሪ እያለች ትዳር የመያዝ ጉጉት ነበራትና ትዳር መሰረተች። በጸሃፊነት እንደ ተመረቀችም በግለሰብ ኮምፒውተር ቤት ተቀጥራ በጸሃፊነት መስራት ጀመረች። ስራዋ ግን ከአንድ ዓመት አልዘለለም። ምክንያቱም የራሷን ኮምፒውተር ቤት ስለከፈተች። ከጊዜ በኋላ ይህንንም ስራ ተወችው።
ትዳሯን በተመለከተ ከባለቤቷ ጋር ሁለት ልጆችን አፍርተዋል። ለባለቤቷም ልዩ ፍቅር ነበራት። ትዳሯን ለማጽናትም ብዙ ዋጋ ከፍላለች። ባለቤቷን ለማስደሰት እና ትዳሯ እስከመጨረሻው እንዲሰምር ልጆችን ከመውለድ በተጨማሪ የራሷን ስራ መስራት እንዳለባት ራሷን አሳመነች። ይህን ጊዜ ንግድ የመነገድ ጉጉቷ በእጅጉ ጨመረ።
ታላቅ ወንድሟ የታሸገ ውሃ ማከፋፈያ ሱቅ ከፈተላት። ስራውንም በጥሩ ሁኔታ መስራት ጀመረች። ሱቁን አንድ ዓመት ከሰራች በኋላ የውሃ አቅርቦት እጥረት በመከሰቱ ዘርፉን ቀይራ የመዋቢያ ዕቃዎችና ጥቅም ላይ የዋሉ ልብሶች መሸጫ ሱቅ ከፈተች።
ይህ ስራዋ ጥሩ መስመር ይዞላት እያለ የተከራየችው ሱቅ ባለቤቶች ቤቱን እንደሚፈልጉ ነገሯት። ቤቱንም ለመልቀቅ ተገደደች። ይሄኔ አንድ መላ ዘየደች። ያሏትን ዕቃዎች ተሸክማ በሞተር ብስክሌት እያዞረች መሸጥ። ይህ ለሴት ልጅ አስቸጋሪ ቢሆንም ነገዋን የተሻለ ለማድረግ ዝቅ ብላ መስራት እንዳለባት ተገንዝባለች። በቆራጥነት መስራቱን ተያያዘችው።
ጎን ለጎንም በተለይ በዓላት ሲመጡ እንቁላል በብዛት እየተረከበች እየዞረች ትሸጣለች። ይህ ብቻም ሳይሆን ዶሮን ጨምሮ ሰዎች እንዲቀርብላቸው የሚፈልጉትን ዕቃዎች ሁሉ ከየትም አፈላልጋ አምጥታ ትሸጥላቸዋለች።
በአንድ ወቅት አንድ ጓደኛዋ ስራ አመጣላት። 5 በጎች የሚፈልጉ ሰዎች እንዳሉ ነገራት። ለአፍታም አላንገራገረች። ከሲዳማ ክልል በንሳ አካባቢ በጎቹንና በርካታ እንቁላሎችን አስመጣች። ሐዋሳ ላይ ከተሽከርካሪው ላይ በጎቹን ለማውረድ ሴትነቷ ከዳት። ይሄኔ የተሰማት ስሜት ውስጧን በእልህ ሞላው። እንደምንም ተጋግዛ አወረደች።
በጎቹንና እንቁላሎቹን ለሚፈልጉት ሰዎች አስረከበች። ሌሎች ዕቃዎችንም እንዲሁ እየተዟዟረች መሸጧን ቀጠለች።
ታዲያ ለሽያጭ በእጇ የሸከፈችውን ዕቃ ሁሉ ሰዎች አያሳፍሯትም ይገዟታል። ገድ አላት። ገዢዎቿ ብቻ ሳይሆኑ ለሽያጭ ዕቃ የሚያስረክቧትም ገንዘብ ባትከፍላቸው እንኳን በእምነት ይሰጧታል ሰርተሽ ትከፊያለሽ በሚል። የሚያበድሯትም አልጠፉም። እሷም በብድርም ቢሆን የተረከበቻቸውን ዕቃዎች ያለመታከት አዙራ ትሸጣለች። ያገኘችውን ገቢ ብድሯን ትከፍልበታለች። በጎን ቤተሰቧንም ታስተዳድርበታለች።
አንድ ወቅት ደግሞ ጓደኞቿ ወደ ዱባይ ሄዳ ዕቃ እያመጣች እንድትሸጥ መከሯት። ለንግድ እንዲሆናትም 100 ሺህ ብር አበደሯት። ብሩን እንደተረከበች ግን እንዳትከስር ስጋት ገባት። ጥቂት ከራሷ ጋር ከመከረች በኃላ አነስተኛ ምግብ ቤት ለመክፈት ተሰናዳች። ይህን ስራ ስትጀምር በወር 1 ሺህ 200 ብር የተከራየችበት ክፍል አመቺ አልነበረም። ግድግዳው ተቦድሶ፣ በሩ ተነቃቅሎ በእጅጉ ቆሽሾ ነበር። በሚገባ አጽድታ ስራዋን ጀመረች።
ይህን ጊዜ ግን ያኔ በተስፋ ተሞልታ እንዲጸና ዋጋ የከፈለችለት ትዳር ሳይሰምር ቀረ። ልጆቿን ይዛ ወጥታ የራሷን ኑሮ መኖር ጀመረች። ፈተና ቢበዛባትም አሁንም ተስፋ አልቆረጠችም። ችግሯ ጊዜያዊ እንደሆነ አምናለች። ፊቷን አዲስ ወደ ጀመረችው ስራ አዞረች። የተከራየችውን ክፍል ለማጽዳት 30 ሺህ ብር ወጪ አደረገች።
ይሄኔ ወዳጆቿ ሁሉ ምግብ ቤት ሰርታ ስለማታውቅ እንዳትከስር በመስጋት እንድትተው ጎተጎቷት። እሷ ግን በእምነቷ ጸናች። ምግብ ቤቱን ስትጀምር እርሷ ጥቂት ግብዓቶችን ነው የተጠቀመችው። ከገንዘብ ጀምሮ ጨው፣ በርበሬ፣ ለስላሳና ሌሎች ግብዓቶችን በሚችሉት ልክ ድጋፍ ያደረጉላት ወዳጆቿ ነበሩ። ይህም ይበልጥ አበረታት። ወገቧን ጠበቅ አድርጋ ከአንድ ሰራተኛ ጋር ምግብ ቤቱ መከፈቱን አበሰረች።
ዛሬ ለደረሰችበት ከፍታ መሰረት የሆናት “ሰሊና ፋስት ፉድ” ያኔ ተወለደ። ለስራዋ ባላት ፍቅር እንደ ቢሮ ሰራተኛ ዘንጣ ነበር ስራዋን የምትሰራው። ዝቅ ብላ መስራት ያለባትንም ሁሉ ትሰራለች። መቼም ስራ ነውና መጥበሻ እያቃጠላት፣ ትኩስ ዘይት እላዩዋ ላይ እየተደፋባት ጥርሷን ነክሳ መስራቷን ቀጠለች። የምታለቅስባቸው ቀኖችም ነበሩ።
ቀስ በቀስ ስራውን ለመደችው። ከቆይታ በኋላ ከጎን አንድ ክፍል ቤት ተለቀቀ። መኖሪያዋንም በዚያ አደረገች። አንድ ምሽት ግን ከባድ ዝናብ ዘንቦ ጎርፍ በበሩ ስር ገብቶ ቤቷን አጥለቀለቀው። ይሄኔ ሌሊቱን ሙሉ ቆማ አሳለፈች።
መለስ ቀለስ እያለ ፈተና ቢያስቸግራትም ስራዋን በትጋት ቀጠለች። የኮቪድ ወረርሽኝ ሊከሰት አካባቢ ዱባይ ሄዳ ዕቃ እያመጣች ጎን ለጎን መሸጥ ጀመረች። ነገሮችም መልካቸውን ያዙ። ከስራዋ በተጓዳኝ ልጆቿን ምንም ሳይጎድልባቸው ታስተምራቸዋለች።
ከዚያም የምግብ ቤቷን ሰራተኞች ቁጥር ወደ 9 አሳደገች። አሁንም ከጎኗ ቤት ሲለቀቅ በመደዳ 3 ክፍሎችን ይዛ ስራዋን አስፋፋችው። እንዲህ እንዲያ እያለ ሰሊና ፋስትፉድ በአካባቢው ተወዳጅ ሆነ። ብርቱዋ ሰላማዊትም ራሷን በዚህ መገደብ አልፈለገችም። እዚያው አካባቢ ብዙም ለንግድ ባልተለመደ ቦታ ሌላ ምግብ ቤት ለመክፈት ወጠነች።
ቀዝቀዝ ያለ አካባቢ በመሆኑ በዚህም ጊዜ እንዳትከስር በሚል ፍራቻ ብዙዎች ተቃወሟት። እሷ ግን በአንድ ወዳጇ አበረታችነት አንድ ሙሉ ግቢ ተከራይታ ለስራው አመቺ በሚሆን መልኩ አሳድሳ ካጠናቀቀች በኋላ ምግብ ቤት ጀመረች። ሌላ በሐዋሳ ከተማ ተወዳጅ የሆነ “ሰሊና ቃተኛ” ምግብ ቤት ተወለደ።
ምግብ ቤቱ ተወዶላት በርካታ ደንበኞችን ማፍራት ቻለች። ይህም ከተከፈተ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል። ስትከፍተው እጇ ላይ የነበራት 400 ሺህ ብር ብቻ ነበር። አጠቃላይ የፈጀባት ወጪ ደግሞ 1 ሚሊየን ብር ነው። ነገር ግን ተግታ በመስራት ዕዳዋን ከፍላ አጠናቃለች ማለት ይቻላል።
በአሁኑ ወቅት በመጀመሪያው ምግብ ቤቷ 5 ሰራተኞች፣ በሁለተኛው ደግሞ 11 ሰራተኞች በስሯ አሉ። የምግብ ደንበኞቿ አብዛኞቹ ስፖርተኞች በመሆናቸው ከተመገቡ በኋላ እግረ መንገዳቸውን አረፍ እንዲሉ እዚያው አካባቢ እንግዳ ማረፊያም ከፍታለች።
በሐዋሳ ከተማ ጨፌ በሚባለው አካባቢ ደግሞ መሬት ገዝታ መኖሪያ ቤት ገንብታለች። በብዙ የተፈተነው የሰላማዊት ታደሰ ሕይወት ዛሬ ላይ ወደ ስኬት እያመራ ይገኛል። ከራሷ አልፋ ለሌሎች ተርፋለች። “ለዚህ ሁሉ ውጤታማነት መብቃቴ የእግዚአብሄር እርዳታ ነው” ትላለች።
“እግዚአብሄርን መፍራቴ ለዚህ አብቅቶኛል። ከትክክለኛው ውጪ አንድም ቀን ያልሆነ መንገድ መርጬ አላውቅም። እያገኘሁ ያለሁት የላቤን ፍሬ ብቻ ነው።” ስትልም የስኬቷን ምስጢር ትናገራለች። በሚገጥሟት ፈተናዎች ሁሉ መቼም ተስፋ እንደማትቆርጥና ስራዋ ባይሳካ እንኳን ዝቅ ብላ ሰርታ መለወጥ እንደምትችል ታምናለች።
ከዚህ ባሻገር የባለቤቷን እጅ ሳትጠብቅ ስራ ለመስራት በድፍረት መነሳቷ ጥንካሬ እንደሆናት ትናገራለች። ከዚህም መነሻ ሴቶችን ስትመክር:-
“ትዳር ውስጥ ሆናችሁ የባሎቻችሁን እጅ ከምትጠብቁ ወጥቶ መነገድን ልመዱ። እኔ ዝም ብዬ ቁጭ ብል ኖሮ ዛሬ የደረስኩበት ደረጃ አልደርስም ነበር። ከዚያ ውጪ ዝግጅቱ ካለ ንግድን በድፍረት መጀመር ያስፈልጋል። በድፍረት ከተሰራ መለወጥ ይቻላል” ትላለች።
ታታሪዋ ወጣት ጉዞዋ በዚህ ያበቃ አይመስልም፡፡ አሁንም የያዘችውን ስራ አስፋፍታ መስራት ትፈልጋለች፡፡ ይህ ውጥኗ እንዲሰምር ግን የመስሪያ ቦታ ችግር ስለገጠማት የሚመለከታቸው አካላት ችግሯን እንዲቀርፉላት አበክራ ትጠይቃለች፡፡
ሰላማዊት ታደሰ በሕይወቷ ትልቅ አሻራ ላሳረፉት ለቤተሰቦቿ፣ ለጓደኞቿና አብረዋት ለነበሩ ሁሉ ምስጋናዋን አቅርባለች።
More Stories
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው
“የችግር ቀናቶቼን አልረሳቸውም” – ወጣት አያኖ ብርሃኑ