“የታሪፍ ችግርን ለመፍታት በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር ተዘርግቷል” – አቶ አዳነ አየለ

“የታሪፍ ችግርን ለመፍታት በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር ተዘርግቷል” – አቶ አዳነ አየለ

የሳምንቱ የንጋት እንግዳችን አቶ አዳነ አየለ ይባላሉ፡፡ በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ ናቸው፡፡ ትውልዳቸው በሲዳማ ክልል፥ መልጋ ወረዳ ነው፡፡ ከ5ኛ ክፍል ጀምሮ 2ኛ ደረጃ ትምህርት እስካጠናቀቁበት ድረስ በሀዋሳ ከተማ ተምረዋል፡፡ የመጀመሪያ ድግሪ በሂሳብ ትምህርት እንዲሁም የ2ኛ ድግሪ በትምህርት አመራርና አስተዳደር በዲላ ዩኒቨርስቲ እንዲሁም በኢኮኖሚክስ 2ኛ ድግሪ አላቸው፡፡

ከእንግዳችን ጋር በሀዋሳ ከተማ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ

በደረጀ ጥላሁን

ንጋት፦ የንጋት እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ በመሆንዎ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡

አቶ አዳነ፦ እኔም ለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡

ንጋት፦ የሀዋሳ ከተማ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

አቶ አዳነ፦ በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ስምንት ክፍለ ከተማና 32 ቀበሌያት አሉ። ከነዚህ ውስጥ 12ቱ የገጠር ቀበሌያት ናቸው። በሁሉም ክፍለ ከተማና ቀበሌያት ደረጃቸውን የጠበቁ የአስፓልትና የጠጠር መንገዶች አሉ፡፡ በሌላ በኩል የተከፈቱ ግን ቀሪ ሥራ የሚጠብቃቸው መንገዶች አሉ፡፡ እነዚህም በከተማ አስተዳደሩ የተሰሩ ሲሆን በገጠር ቀበሌያት ያሉት በገጠር ተደራሽ መንገድ የተሰሩ ናቸው፡፡ በገጠር ቀበሌያትም ቢሆን የኢኮኖሚ ፋይዳ ያላቸው ትላልቅ መንገዶች በከተማ አስተዳደሩ የሚሰሩ ናቸው። በእነዚህ መንገዶች የተሽከርካሪ ስምሪት ተሰጥቶ ህብረተሰቡ እየተገለገለበት ይገኛል፡፡

ስምሪቱ በሁለት መንገድ የሚከናወን ሲሆን አንደኛው የከተማ ትራንስፖርት በከተማው የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን ይሸፍናል። በዚህ የሚካተቱት የከተማ አውቶቡሶች ሲሆኑ እነሱም ከተማውን ሸፍነው ይንቀሳቀሳሉ። ሌላው ከባለሶስት ጎማ ባጃጅ ጀምሮ ዳማስ፣ ሱዚኪ፣ ኩዊት እና ሚኒባስ በዚህ አገልግሎት የሚሳተፉ ናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ደረጃ ሶስት አሟልተው እና ከደረጃ ሶስት ዝቅ ያሉ ተሽከርካሪዎች ደግሞ መመሪያው ስለሚፈቅድ ወደ አገልግሎት ይገባሉ፡፡

ሁለተኛው የህዝብ ትራንስፖርት ሀገር አቋራጭን አካቶ በአጎራባች ወረዳዎች እና ከተሞች ከሁለቱ መናኻሪያዎች የሚወጡና የሚገቡ ተሽከርካሪዎችን የሚያካትተው አገልግሎት ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ህግ፣ ሥርዓት፣ ደንብና አሰራር የማስጠበቅ ሥራ ከእኛና ከትራፊክ ፖሊሶች የሚጠበቅ ስለሆነ መንገዱንና ትራንስፖርቱን አቀናጅተን እየሰራን እንገኛለን፡፡

በዚህ ሂደት በተለይ ከተማ ውስጥ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሚበዛባቸውን ለይተን በተቻለ መጠን እንግልት እንዳይኖር እየተሰራ ነው፡፡ ለዚህም በሁሉም መንገዶች ተሽከርካሪዎች እንዲሰማሩና ታሪፍ እንዲወጣላቸው ተደርጎ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

ንጋት፦ ከታሪፍ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የተሰሩ ሥራዎች ምንድናቸው?

አቶ አዳነ፦ የታሪፍ ጉዳይ በተደጋጋሚ የሚነሳ ቅሬታ ነው፡፡ በመሆኑም ከሚመለከታቸው ጋር በመነጋገር ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሄ ስናስቀምጥ ቆይተናል፡፡ ችግሩ በሁለት ምክንያቶች ሳይቀረፍ ቆይቷል፡፡ አንዱ ችግር በየጊዜው ታሪፍ እየተጠና ተሳፋሪው እንዲያውቅና በታሪፉ መሠረት እንዲገለገል አቅጣጫ ይቀመጣል፡፡ ከዚህ አንፃር የሚገጥመው ነገር ለህግ ተገዢ ተገልጋይ እንዳለ ሁሉ ግድ የሌለው መኖሩ ነው፡፡ ለትንሽ ገንዘብ ብላችሁ አንከፍልም አትበሉ በሚል የሚቀርቡ ሀሳቦች ህግ እንዳይከበር ያደርጋሉ፡፡ ይህን ለማስወገድ መምሪያው ከባህላዊ አሰራር በመውጣት በከተማ ህዝብ ትራንስፖርት የቴክኖሎጂ ቁጥጥር ሥራዎች እየተሰራ ነው፡፡ ይህም በአሮጌው መናኻሪያ ተግባራዊ በመሆኑ ማንኛውም ተሳፋሪ ከረዳት ጋር ንክኪ ሳይኖረው የማስተናገድ ተሞክሮውን ለማስፋት እየተሰራ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል ወደ ከተማ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ቴክኖሎጂው ካልደረሰባቸው ዞኖችና ወረዳዎች የሚመጡ ስላሉ ሙሉ በሙሉ ችግሩን ማስቀረት አይቻል ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ ጅማሮ ስላለ በሂደት ይስተካከላል ብዬ አስባለሁ፡፡

ታሪፍ በከተማ ውስጥ በየጊዜው ከወቅቱ የነዳጅ ዋጋ አንፃር እየታየ እየተሻሻለ የሚመጣ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንዶች በተወሰነው ታሪፍ መሠረት አንደማያስከፍሉ ይስተዋላል። የታሪፍ ችግርን ለመፍታት በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር ተዘርግቷል። ባጃጅን ጨምሮ በሁሉም ታክሲዎች ላይ QR CODE የመለያ ምልክት እንዲለጠፍ ተደርጓል። አጠቃቀሙም ተሳፋሪው እስካን በማድረግ የት መስመር እንደሚሄድ ስንት እንደሚከፍል በቴክኖሎጂው ማየት ይቻላል፡፡ ይህም ሌብነትን ጭምር የሚያስቀር ነው፡፡

በተሽከርካሪ የታገዘ ዝርፊያን ቴክኖሎጂው የሚያስቀር ነው፡፡ ሌላው ተሳፋሪው ስካን ሲያደርግ መረጃው ወደ ዋናው ቋት ሲስተም ይተላለፋል፡፡ ይህም ተሳፋሪው መቼ እና ወዴት እንደተሳፈረ እንዲሁም በየትኛው ተሽከርካሪ እንደተሳፈረ እና የተሽከርካሪውን ማህበር ሁሉ ለማወቅ ይረዳል፡፡ ለቤተሰብም መረጃውን መላክ ይቻላል፡፡ በዚህ መልክ የጠፋ ነገር ካለ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል፡፡

ይህ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ቴክኖሎጂ ከመቆጣጠርና በተሳፋሪው በኩልም የአጠቃቀም ችግር መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ በኛም በኩል ትራፊክ ፖሊሶች ተሽከርካሪን በማስቆም ክፍያውን ከመጠየቅና ሥርዓት ከማስያዝ አንፃር ክፍተቶች ይስተዋላሉ። በቀጣይ ከምንሰራቸው ሥራዎች አንዱ በታሪፍ እና ተገልጋይን ማርካት ጉዳይ ላይ በመሆኑ አሰራራችን በኃላፊነትና በተጠያቂነት መወጣት ስንችል ችግሩን እንቀርፋለን፡፡

ንጋት፦ የባለ ሶስት እግር ባጃጅ ከመስመር እየወጡ መምጣት መነሻው ምንድነው

አቶ አዳነ፦ ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ ባጃጅ በከተማው በማህበራት ተደራጅተው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ የተሽከርካሪዎቹ ህጋዊነት ከተረጋገጠ በኋላ ይሰማራሉ፡፡ በተሰጣቸው መስመር እያንዳንዱ ማህበር አባላቱን የማሰማራት ግዴታ አለበት፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ እንዳይሰሩ የሚከለከልባቸው መስመሮች አሉ፡፡ መስመሩ በርካታ ተሽከርካሪዎችን የሚያስተናግድ ከሆነ፣ በዋናነት ከተማውን አቋርጦ የሚያልፈው መንገድና ሌሎችም የትራፊክ መጨናነቅ ያለባቸው መንገዶች ላይ እንዳይሰሩ ተደርጓል፡፡ ባጃጆች በትራንስፖርት ረገድ ችግርን የሚፈቱ መሆናቸው ይታወቃል። ይሁን እንጂ የተከለከሉት መንገዶች የተሽከርካሪ ፍሰቱ ከፍተኛ በመሆኑ ተደጋጋሚ አደጋ ስለሚያጋጥም ይህን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ግን በሌሎቹ መንገዶች ላይ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

ንጋት፦ በከተማው የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ምን ያህል ናቸው?

አቶ አዳነ፦ በከተማው አጠቃላይ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች በማህበር ተደራጅተው ይሰራሉ፡፡ በድጋፍ ደረጃ የሚሰሩ ሚኒባሶች አሉ፡፡ ነገር ግን በከተማው መምሪያ በኩል ፈቃድ አግኝተው የሚሰሩ 15 ማህበራት ናቸው፡፡ አንዱ ማህበር 300 ተሽከርካሪዎችን ይይዛል፡፡ ባጠቃላይ 4 ሺህ 500 የሚሆኑ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

ንጋት፦ መንገዶች በተለይ ቦይ ለመስራት ተብሎ ተቆፋፍረው ይታያሉ፡፡ በጊዜ ያለመጠናቀቃቸው ምክንያት ምንድነው ይላሉ?

አቶ አዳነ፦ ትራንስፖርትና መንገድ ሲባል አንዳንዶች የመንገድ ግንባታ ጭምር ተቋሙን የሚመለከት ይመስላቸዋል፡፡ የመንገድ ግንባታው፣ ቁጥጥሩ፣ አስተዳደርና ጥገና በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን የሚታቀፍ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከተማው ላይ እንደሚሰራ አካል ችግሩን አውቀዋለው፡፡ የመጀመሪያው የዲዛይን ችግር ነው፡፡ ዲዛይን ሲጠና እያንዳንዱ ዲች /ቦይ/ ውሀ የመያዝ አቅሙ እንዲሁም በክረምት ወቅት የሚዘንበውን የዝናብ መጠን ታሳቢ አድርጎ ከመስራት አኳያ ክፍተት አለበት፡፡ የዲዛይን ችግር በስፋት እንደሚታይ ተገምግሟል፡፡

ስለዚህ አሁን ላይ በከተማው የሚታዩ የተቆፈሩ ዲቾች ቀድሞ የነበሩ ዲዛይኖች ፈርሰው የውሃውን አቅም ሊቋቋም የሚችል ሥራ ለመስራት ታስቦ የተካሄደ ነው፡፡ ሌላው የደለል መሙላት ችግር ከመከሰቱ በፊት የመጥረግ ሥራ ያለመስራት ጉድለት ነበር። እነዚህ ተደማምረው ነው ችግር የሆኑት። እነዚህም እየታረሙና እየተስተካከሉ ይገኛል።

ንጋት፦ የትራፊክ አደጋን ከመቀነስ አኳያ ምን እየተሰራ ነው?

አቶ አዳነ፦ ሁሌም በስፋት የማስተማር እና የመቀስቀስ ሥራ የምንሰራው የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ነው፡፡ በ2015 ዓ/ም 67 ሰው በትራፊክ አደጋ ተጎድቶብናል፡፡ ከነዚህም 37 ሰዎች የሞት፣ ቀሪው ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡ የንብረት ውድመትም አጋጥሟል፡፡ ይህ ቀላል አይደለም፡፡ ሀገርን የሚጎዳ ነው፡፡

ለትራፊክ አደጋ መንስኤው በአሽከርካሪ እና እግረኛ ላይ የሚታይ ችግር ሲሆን እግረኞች ጥንቃቄ አድርገው መጓዝ አለባቸው፡፡ አሽከርካሪውም ለእግረኛ ቅድሚያ መስጠት እና በጥንቃቄ መጓዝ አለበት፡፡ ለዚህም በየእምነት እና በማህበራዊ ተቋማት እንዲሁም በተለያዩ ሁነቶች ላይ በመገኘት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተሰራ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በየትምህርት ቤቱ ክበባትን በማደራጀትና ያሉትንም በማጠናከር የቅድመ ጥንቃቄ ሥራውን እየሰራን እንገኛለን።

ንጋት፦ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ምን እየተሰራ ነው?

አቶ አዳነ፦ በከተማው 12 የሚሆኑ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት ይገኛሉ። እነዚህን የመቆጣጠርና የማስተዳደር፣ ሲያጠፉ የመጠየቅ ሥራ ይሰራል፡፡ በዚህ መነሻ ድጋፉ እንደተጠበቀ ሆኖ ብቃት፣ አቅምና ችሎታ ያላቸውን አሽከርካሪዎች አሰልጥነው እንዲያወጡ ነው የሚፈለገው። ብቃታቸው በንድፈ ሀሳብና በተግባር ይፈተሻል፡፡ የንድፈ ሀሳብ ፈተና ቀደም ሲል የፈተና አሰጣጥ ሥርዓቱ ጠንካራ አልነበረም፡፡

ይህን ለመቀየር ከፌደራል ተሞክሮዎችን በማምጣት ተግባራዊ አድርገናል፡፡ ስለዚህ በንድፈ ሀሳብ የሚያልፉ በትክክል የተረዱ ብቻ ናቸው፡፡ ገንዘብ ሳይሰጥ አይታለፍም የሚለው አስተሳሰብ እየተለወጠ መምጣቱን መረጃው ያሳያል፡፡ የመስክ ላይ ፈተናን በተመለከተ በሰለጠነ ባለሞያ በትራፊክ ኮምፕሌክስ አማካይነት የሚከናወን ነው፡፡ እኛ ጋ ግን መንዳት ብቻ ነው፡፡ ይህም ችግሮች ያሉበት ነው፡፡

ከዚህ አኳያ ትራፊክ ኮምፕሌክስ ሁሉን ነገር በካሜራ የታገዘ በመሆኑ ሌብነቱን የሚያስቀር ነው፡፡ አሁን ላይ ይህ ባይተገበርም በቀጣይ ሥራ የሚሰራ ነው፡፡ በሀገር ደረጃ በሁሉም ክልል በቅርቡ ተግባራዊ የሚደረግ እኛም ተጠቃሚ ስንሆን ችግሩ ይቀረፋል፡፡

ንጋት፦ ቀረ የሚሉት ሀሳብ ካለዎት

አቶ አዳነ፦ ተሽከርካሪዎች ጠቀሜታቸው አጠያያቂ ባይሆንም በከተሞች ለምናደርገው ጉዞ በእግር እና በብስክሌት መጓዝ መልመድ አለብን፡፡ እንቅስቃሴ ማድረግ ለጤና በተለይ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ለመቋቋም ይረዳናል፡፡ አሁን አሁን ያደጉ ሀገራት ልምዱን እየቀየሩት ይገኛሉ፡፡ በከተሞች አካባቢ በብስክሌት መንቀሳቀስ ተለምዷል፡፡

ሀዋሳ የምትታወቀው በብስክሌት ተጠቃሚዎቿ ነበር፡፡ ይህን እንዲመለስ እንፈልጋለን፡፡ የትራንስፖርት አማራጭ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለጤናችንም ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር የነዳጅ ዋጋ በየጊዜው እያሻቀበ በመሆኑ በከተማ የእግር ጉዞና የብስክሌት ተሽከርካሪን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ወጪን ይቀንሳል፡፡ እንዲሁም የአየር ብክለትን እንቀንሳለን፡፡

አሁን ላይ በከተማችን ለብስክሌት የሚሆን መንገድ ተሰርቷል፡፡ ይህን እያሰፋን እንቀጥላለን፡፡ በከተማው በሳምንት አንድ ቀን ሰው በእግርና በብስክሌት እንዲንቀሳቀስ ዋና ዋና መንገዶች መዝጋት ተጀምሯል፡፡ በዚህ እንድንጠቀም አደራ እላለሁ፡፡

ንጋት፦ ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡

አቶ አዳነ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡