የበዓሉ ታሪካዊ ዳራ
በመሐሪ አድነው
መስቀል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሃይማኖታዊ ሥነ ስርዓት አስተምህሮ መሠረት እጅግ ትልቅ ስፍራና ክብር ያለው ነው በማለት በሐዋሣ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ስብከተ ወንጌል ክፍል ሃላፊ አባ መልከፀዴቅ ገብረ ሥላሴ ይገልፃሉ፡፡ እርሳቸው እንዳሉት መስቀል ማለት በመንፈሳዊ “መከራ” የሚለውን ትርጉም የሚሰጥ ሲሆን፥ መስቀል በብሉይ ኪዳንና በአዲስ ኪዳን የተለያዩ ታሪኮች ናቸው ያሉት።
በብሉይ ኪዳን ዘመን ሮማውያን ሃጢአተኛ ወይም ወንጀለኛ ብለው የሚያስቡትን ሠው ከደበደቡ፥ ከቀጡና ብዙ መከራ ካደረሱበት በኋላ ይህ ብቻውን በቂ አይደለም በመስቀል ሊሰቀል ይገባዋል ብለው መከራን ያፀኑበት ነበር፡፡ በዚህም አባ መልከፀዴቅ ወንበዴዎች የሚሰቀሉበት፣ የሚሰቃዩበትና መከራን የሚቀበሉበት ነው ብለዋል፡፡ እስራኤላውያን በምርኮ በሮማውያን አገዛዝ ሥር በነበሩበት ጊዜ ይህን ባህል ወደ እስራኤል ይዘው መጥተው አይሁዳውያንም ወንጀለኛ ብለው ያሰቡትን ሠው በመስቀል ስቅላት ለመቅጣት ይጠቀሙበት ነበር ተብሏል፡፡
መስቀል በብሉይ ኪዳን ደግሞ የተለየ ይዘት እንዳለው አባ መልከፀዴቅ የጠቀሱ ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳም በሠጠው ተስፋ መሠረት ከ5 ሺህ አምስት መቶ ዘመን በኋላ ወደዚህ ዓለም መጥቶና ተገልጦ፥ ከድንግል ማርያም ተዋልዶ 33 ዓመት ከሶስት ወር ወንጌል መንግስትን ከሰበከና ካስተማረ በኋላ የሠው ልጆችን መዳን በማወጅ የሠውን ልጅ መዳን ያከናወነው በመስቀል ላይ ነው። በመሆኑም የመስቀል ታሪክ የተቀየረው ከዚህ ጊዜ በኋላ ነው፡፡ በዚህም መስቀል ላይ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ፈሷል፣ ሥጋው ተቆርሷል፡፡
ለ5 ሺህ 500 ዘመን የአዳም ልጅ በዲያብሎስ ሲረገጥና ሲቀጠቀጥ ከነበረበት ክርስቶስ በመስቀል ላይ በከፈለለት ውድ ዋጋ ነፃ ወጥቷል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሠው ልጆችን ጥንተ ጠላት ዲያብሎስን ድል አድርጐ ክብሩንና አምላክነቱን የገለጠበትና ለሠው ልጆች ያለውን ፍቅር ያሳየበት በመሆኑ በአዲስ ኪዳን መስቀል የክርስቲያኖች የነፃነት አርማ እና የድል ምልክት ተደርጐ ይታያል፡፡
በአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማህፀነ ዮርዳኖስ በአርባ እና በሠማኒያ ቀን የተጠመቁ ክርስቶሳውያን፥ ኦርቶዶክሳውያን መስቀል ሃይላቸው ነው፡፡ የሚታየውንም የማይታየውንም፣ ረቂቁንም ግዙፉንም ጠላትን ድል የሚያደርጉት በመስቀል ምልክት ነው፡፡ በመፅሐፍ ቅዱስ እንደተፃፈ መስቀል ሃይላችን ነው፣ መስቀል መድሃኒታችን ነው፣ የነፍስና የሥጋችን መዳኛ ነው እንላለን ያሉት አባ መልከፀዴቅ፣ አስከትለውም በመስቀል ላይ በተከፈለ ዋጋ የእኛ ህይወትና ድነታችን ተረጋግጧል ማለታችን ነው በማለት አብራርተዋል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቅዱስ መፅሐፍ እንደገለፀው “ክርስቶስ ጥልን በመስቀል ገደለ በሠው ልጆችና በእግዚአብሔር መካከል፣ በሠው ልጆችና በመላእክት መካከል፣ በህዝብና በአህዛብ መካከል፣ በነፍስና በሥጋ መካከል በሠማይና በምድር መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ በመስቀሉ ድል አደረገ፡፡ አፈረሰ” ብሎ ይናገራል፡፡ ስለሆነም ይላሉ አባ መልከፀዴቅ መስቀል በእኛ በኦርቶዶክሳውያን አስተምህሮና በቤተክርስቲያናችን ሥርዓት እጅግ ልዩ ቦታ ያለው ነው ይላሉ፡፡ አንድ የሀገር ወታደር ዳር ድንበርን ለመጠበቅ ወደ ጦር ሜዳ በሚዘምትበት ጊዜ ትጥቁን አሟልቶ እንደሚሄድ ሁሉ ኦርቶዶክሳውያንም በየትኛውም የክርስትና ዓለምም ለክርስትና ህይወት በሚሠማሩበት ሠዓት ዓርማና ምልክት አድርገው ጠላታቸውን ድል የሚያደርጉበት በመስቀሉ ምልክት ስለሆነ ያለመስቀል አይንቀሳቀሱም ብለዋል፡፡
አባ መልከፀዴቅ እንደገለፁት መስቀልን በማህተባችን እናስረዋለን፣ በእጃችን እንይዘዋለን በግንባራችንና በተለያዩ ሥፍራዎች ምልክት አድርገን እንጠቀመዋል። ነገር ግን ይህን የምናደርገው መስቀል በብሉይ ኪዳን ያለውን ታሪክ አስበን አይደለም፡፡ ይልቁንም በሐዲስ ኪዳን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተሰቀለ በኋላና የመስቀል ታሪክ ከተቀየረ ወዲህ በመስቀል የተሰጠንን ድነትና የተደረገልንን ነገር ካወቅን በኋላ የምናደርገው ምልክት ነው በማለት አስገንዝበዋል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ስጋውን የቆረሰበት ደሙን ያፈሰሰበት መስቀል ብዙ ተአምራትን ሲያደርግ ኖሯል፡፡ እውራንን ሲያበራ፣ በሽተኞችን ሲፈውስ ፣ ለምፃሞችን ሲያነፃና ጐባጦችን ሲያቀና እንደነበር ይነገራል።
በዚህም ምክንያት ቀደም ብሎ በመስቀል ላይ መድሃኒትዓለምን የሰቀሉት ክፉና ምቀኛ አይሁዳውያን ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል አሁን ተአምራትን ያደርጋል ብለው ከሶስት መቶ አመታት በላይ ጉድጓድ ቆፍረው ቀብረውታል፡፡ ከሶስት መቶ ዘመን በላይ ተቀብሮ የነበረውን የክርስቶስ መስቀል ታዲያ አንዲት እግዚአብሔርን የምትፈራ እሌኒ የተባለች መንፈሳዊት ሴት እግዚአብሔር አስነስቶ የተደበቀው፣ የተሰወረውና የተቀበረው መስቀል እንዲገኝ ሆኗል፡፡ ዛሬም እንደምናየው ሠዎች ሠላምን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ አብሮነትንና ኢትዮጵያዊነትን ለመቅበር ጥረት ያደርጋሉ። ምንም እንኳን ኢትዮጵያዊ እሴቶታችንን ለመቅበር የሚደረግ እንቅስቃሴዎች ቢኖሩም እግዚአብሔር በጊዜው እንደ እሌኒና ቆስጤንጢኖስ አይነቶቹን ሰዎች አስነስቶ እውነትነት እንደሚያወጣ እምነታችን ነው ብለዋል አባ መልከፄዲቅ፡፡ አይሁድ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታ በመቅበር እንዲረሳ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ በ326 ዓ.ም የንጉሥ ቆስጤንጢኖስ እናት ንግስት እሌኒ ቅዱስ መስቀሉን ለመፈለግ ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ አደረገች፡፡
እዚያም ደርሳ ጉብታ የሆነውን ሁሉ ብታስቆፍር መስቀሉ ያለበትን ቦታ ለማግኘት አልቻለችም፤ ሠውም ብታስጠይቅ የሚያውቅ አልተገኘም፡፡ በመጨረሻም የመስቀሉ መገኘት የእግዚአብሔር ፍቃድ ነበረና አንድ አይሁድ አረጋዊ ታሪክ አዋቂና ሽማግሌ አግኝታ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበትንና የተጣለበትን አካባቢ ያውቅ እንደሆነ ጠየቀችው፡፡ ሽማግሌውም “አንቺም በከንቱ አትደክሚ ሠውንም አታድክሚ እንጨት አሰብስበሽ እጣን ጨምሪበት፡፡ በእሳትም አያይዘው የአጣኑ ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ ወደ ታች ሲመለስ አቅጣጫውን አይተሽ አስቆፍሪው፡፡ በዚህ ምልክት ታገኚዋለሽ” አላት፡፡ እርሷም ያላትን ሁሉ አደረገች፡፡ እንጨት ደምራ በዚያ ላይም እጣን ጨምራ በእሳት ለኮሰችው፤ የእጣኑ ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ ወደ ታች ሲመለስ መስቀሉ ያለበትን ቦታ በጣት ጠቅሶ እንደማሳየት ያህል አመለከተ፡፡
ንግስት እሌኒም ጢሱ ያረፈበት ቦታ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበት እንደሆነ አመነች፡፡ ይህ አይሁድ አረጋዊ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ በኋላ በክርስቶስ አምኖ ተጠምቋል። ሥሙም ክርያኮስ መባሉን አባ መልከፀዴቅ ነግረውናል፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ የመስቀልን በዓል ደመራ በመደመርና ችቦ በማብራት፣ ቅዳሴ በመቀደስና ማህሌት በመቆም የምናከብረው ለዚህ ነውም ብለዋል፡፡ በዚሁም ላይ አባ መልከፀዴቅ አክለው ሲናገሩ ይህን ታላቅ ዕፀ መስቀል በወቅቱ የነበሩ ታላላቅ ነገስታት የሚያደርጋቸውን ተአምራት በማየት ለእያንዳንዳቸው ይደርሳቸው ዘንድ በአራት ተከፍሏል፡፡
ከአራቱ አንዱ የቀኝ እጁ ያረፈበት ግማድ /ክፋይ/ በሀገራችን ኢትዮጵያ በደብረ ከርቤ ግሸን ማርያም ሲገኝ ሌሎች ሶስቱ ግን የት እንደደረሱ አይታወቅም ብለዋል፡፡ የታላቋን ንግስት እሌኒን ታሪክ በማስታወስ መስከረም 17 የመስቀል በዓል ይከበራል ያሉት በሐዋሣ ቅ/ገብርኤል የስብከተ ወንጌል ክፍል ሃላፊ አባ መልከፀዴቅ ለመላው ክርስቲያኖች እንኳን ለጌታችንና ለመድሃኒታተን የመስቀል በዓል አደረሳችሁ በማለት የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
More Stories
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው
“የችግር ቀናቶቼን አልረሳቸውም” – ወጣት አያኖ ብርሃኑ